ሄሎ ሀበሻ ምርጥ የሀበሻ መዝናኛ ሰፈር፣
ይህ ዌብ ሳይት ሀበሻን ከመላው አለም በማገናኘት የሚያወያይ
የሚያዝናና ዌብ ሳይት ወይም መድረክ ነው፥፥
ተሳተፉ ፣ ኮመንት አድርጉ ፣ የራሳችሁን ፃፉ
0 users browsing Religion. | 1 guest
Pages: 1
Posted on 02-12-17, 07:14 pm


Karma: 90
Posts: 226/879
Since: 02-29-16

Last post: 69 days
Last view: 69 days
‹ላይክ› እና ‹ሼር

አንድ አባት ነበሩ፡፡ ይህ ሕዝብ እግዚአብሔርን ቢያየው ኖሮ ያምንበት ነበር፤ በእምነቱም ይጸና ነበር ብለው
ያስባሉ፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር ለሰው መገለጥ አለበት ብለው ያምናሉ፡፡ ይህንንም ሃሳባቸውን ደጋግመው
ለእግዚአብሔር ይነግሩት ነበር፡፡ ‹ለምን በአብርሃም ዘመን እንደተገለጥከው አትገለጥም› እያሉ ይከራከራሉ፡፡
ሃሳባቸው ደገኛ ምኞታቸውም ቅን ነበርና ፈጣሪያቸው መለሰላቸው፡፡ ‹‹እኔ ብገለጥም መጀመርያ ነገር ሰዎች
አያኝም፤ ሁለተኛም ቢያዩኝም አይጠቀሙብኝም›› አላቸው፡፡
እርሳቸው ደግሞ ‹ብዙዎቹ ያውቁሃልና ይጠቀሙብሃል፤ ነገር ገን ዘመኑ ካላየን አለናምንም ስለሚል እየተጠራጠሩ
ነው፤ እባክህ ተገለጥና የሚሆነውን እንየው›› ይሉ ነበር፡፡ አምላክም መልሶ ‹ስለ እኔ ማወቅና እኔን ማወቅ
ይለያያሉ፡፡ ብዙዎች ሃይማኖተኞች ስለ እኔ ያውቃሉ እንጂ እኔን ራሴን አያውቁኝም፡፡ ሃይማኖትኮ ስለ ፈጣሪ
ማወቅ ሳይሆን ፈጣሪን ማወቅ ነው፡፡ ስለ ፈጣሪ ማወቅ ዕውቀት ነው፣ ፈጣሪን ማወቅ ግን እምነት ነው፤ ስለ
ፈጣሪ ማወቅ የሚቻለው በትምህርት፣ ፈጣሪን ማወቅ የሚቻለው ግን በእምነት ነው፡፡ ስለ ፈጣሪ ማወቅ
ያራቅቃል፣ ፈጣሪን ማወቅ ግን ይለውጣል›4ብሎ መለሰላቸው፡፡

እርሳቸው ግን ለብዙ ዘመናት ጥያቄያቸውን አላቋረጡም ነበር፡፡ አንድ ቀንም በሕልማቸው በከተማዋ አደባባይ
ብዙ ሺ ሕዝብ በተሰበሰበበት ቦታ እግዚአብሔር ተገልጦ አዩ፡፡
በመጀመርያ ጋዜጠኞች ተሰብስበው መጡና ‹‹ቃለ መጠይቅ ለማድረግ ይፈቀድልን››4ሲሉ ጠየቁ፡፡ ከመካከላቸውም
አንዳንዶቹ የምናደርገው ቃለ መጠይቅ ‹‹ሐርድ ቶክ›› መሆን አለበት የሚል ሃሳብ ሠነዘሩ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ቃለ
መጠይቃችን በቀጥታ ሥርጭት መተላለፍ አለበት ሲሉ ሞገቱ፡፡ አባ በዚህ በጣም አዘኑ፡፡ ‹‹እግዚአብሔርኮ
የመጣው አግኝታችሁት በነፍሳችሁ እንድትጠቀሙበት እንጂ ለቃለ መጠይቅ አይደለም›› ብለው ተቆጡ፡፡
ጋዜጠኞቹም በዚህ ቅር ስላላቸው እየዛቱ ሄዱና ‹‹እግዚአብሔር ለቃለ መጠይቅ ፈቃደኛ አልሆንም አለ››
‹‹እግዚአብሔርን እንዳናናግር መነኩሴው ተቆጡ›› የሚሉ የዜና ርእሶችን ይዘው ወጡ፡፡
ከእነርሱ በኋላ የመጡትም ሰዎች በዓለም ላይ በጥንት ጊዜ ስለተፈጸሙና አከራካሪ ስለሆኑ ነገሮች እግዚአብሔርን
ለመጠየቅ የሚፈልጉ ምሁራን ነበሩ፡፡ እነዚህ ምሁራን በዓለም ላይ እንዴት እንደተፈጠሩ ግልጽ ስላልሆኑ፣ በመላ
ምት ስለሚታመኑ፣ በቂ ማስረጃ ስላልተገኘላቸው፣ ከሃይማኖት ትምህርት ጋር ስለማይጣጣሙ የሳይንስ ሃሳቦች፣
በድሮ ዘመን ነበሩ ስለሚባሉ፣ ግን ስለጠፉ ነገሮች መጠየቅ እንደሚፈልጉ ለአባ ተናሩ፡፡ ይህ ነገርም አባን እንደገና
አሳዘናቸው፡፡ ‹እግዚአብሔር የመጣበት ዓላማ የእናንተን ምሁራዊ ጥያቄ ለመመለስ አይደለም፤ የነፍሳችሁን ጥያቄ
ለመመለስ እንጂ፤ ይህንንማ በተሰጣችሁ አእምሮ መርምራችሁ ድረሱበት፤ ይልቅ ተመርምሮ የማይደረስበትን
የነፍሳችሁን ነገር ለምን አትጠይቁም›4ብለው አዘኑ፡፡
ምሁራኑም ‹እግዚአብሔር ሳይንሳዊ ለሆኑ ጥያቄዎች መልስ የለውም ማለት ነው››እያሉ እየቀለዱ ተመልሰው ሄዱ፡፡
እነርሱ እንደሄዱም የነገ ሕይወታቸው ዕጣ ፈንታ ምን እንደሆነ ለማወቅ የሚፈልጉ ሰዎች መጡ፡፡ የማገባው ማንን
ነው?ምን ዓይነት ልጅ እወልዳለሁ? ውጭ ሀገር የምሄደው መቼ ነው? በቀጣይ የሀገሪቱ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል?
ስንት ዓመት እኖራለሁ? ከሞትኩ በኋላ የት ነው የምገባው? የሚሉ ሚሊዮን ጥያቄዎችን ይዘዋል፡፡ እግዚአብሔር
የነገውን ጭምር ስለሚያውቅ ይህንን እንዲነግራቸው ተማጸኑ፡፡ አባም እንደገና አዘኑ፡፡ ‹‹የነገውን ዕጣ ፈንታ
ለመንገር እግዚአብሔር አልመጣም፤ የነገውን ዕጣ ፈንታ የምታስተካክሉበትን መንገድ ለማሳየት እንጂ፡፡ የነገውን
ዕጣ ፈንታችሁን ለመንገር ቢመጣ ኖሮ ከእንስሳት ነጥሎ ለምን አእምሮ ይሰጣችሁ ነበር፡፡ ጠንቋይ ቤት ስትሄዱ
የምታቀርቡትን ጥያቄ እንዴት እግዚአብሔር ፊት ታቀርባላችሁ፡፡ የነገ ዕጣ ፈንታችሁ በእናንተ እጅ ነው፡፡
ማሣመርም ማበላሸትም ትችላላችሁ›› አሉና መለሱላቸው፡፡
ሰዎቹም እየተናደዱ ተመለሱ፡፡ ‹‹ታድያ ነገ የምሆነውን ካልነገረኝ እግዚአብሔር ምን ያደርግልኛል››4ይሉ ነበር፡፡
ከእነርሱ ቀጥለውም ከእግዚአብሔር ብዙ ነገሮች የሚፈልጉ ሰዎች መጡ፡፡ ገንዘብ፣ ሚስት፣ ልጅ፣ ሥልጣን፣
የውጭ ዕድል፣ ሥራ፣ ዝና፣ ውበት፣ ቤት፣ መኪና፣ እድሜ፣ ጤና፣ የማይፈልጉት ነገር አልነበረም፡፡ አንዳንዶቹም
የሚሰጣቸው ነገር ከሌሎች የሚበልጥ እንዲሆን ይፈልጉ ነበር፡፡ ሌሎችም የያዙት የፍላጎት ዝርዝር በብዙ
ወረቀቶች የተሞላ ነበር፡፡ አንዱም ሌላው እንዳያይበት ይሸፍነው ነበር፡፡ እርስ በርሳቸውም አይነጋገሩም ነበር፡፡
አንዳንዶቹም ከሚሊዮን በላይ ቁጥር መኖር አለመኖሩን ለማጣራት ይጥሩ ነበር፡፡ የሚጠይቁት በዚያ ልክ ይሆን
ዘንድ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ የረሱት ነገር ካለ እንዳይቀርባቸው ‹ወዘተ›4የሚል ልመና ይዘው መጥተው ነበር፡፡
ይህም አባን በጣም አስገረማቸው፡፡ ‹‹እግዚአብሔርኮ አምላክ እንጂ የርዳታ ድርጅት አይደለም፡፡ እርሱ ይህንን
ሁሉ እንደመና የሚሰጣችሁ እናንተ ምን ሠርታችሁ ልትበሉ ነው? አንዳችሁም እንኳን የሚያስብ ልቡና፣
የሚፈጥር አእምሮ፣ የሚጠበብ ጥበብ ስጠኝ እንዴት አትሉም? እንዴትስ ደግሞ ለራሳችሁ ብቻ የሚያስፈልጋችሁን
ይዛችሁ ትመጣላችሁ? ለሌላውስ? ደግሞስ የጎደላችሁን ብቻ ይዛችሁ ስትመጡ ስላላችሁ ነገር ምነው አንዳች
ምስጋና አልተነፈሳችሁም?›› ሰዎቹም በአባ መልስ ከመበሳጨታቸው የተነሣ ‹‹ታድያ እግዚአብሔር ለችግሬ
ካልደረሰለኝ ለመቼ ሊሆነኝ ነው››4እያሉ ተማርረው ተበተኑ፡፡
እነዚህ ሲወጡ ሌሎች ደግሞ መጡ፡፡ ግማሹ ሞባይል ስልክ፣ ሌላው አይፎን፣ ሌላው አይፓድ፣ ሌላው ደግሞ
ካሜራ ይዟል፡፡ አንዳንዶቹ እግዚአብሔርን ሊጠይቁ ሲጠጉ አንዳች የሆነ ውሳጣዊ ነገር ይኖራቸዋል ብለው አባ
ደስ አላቸው፡፡ እርሳቸውም ጠጋ አሉ፡፡ ወጣቶቹ ግን ‹‹የኢሜይል አድራሻ አለህ፣ ፌስ ቡክ አለህ? ትዊተርስ›› እያሉ
ነበር የሚጠይቁት፡፡ አባ ተገርመዋል፡፡ ሌሎቹም ሞባይላቸውን አውጥተው ስልክ ለመቀበልና ለመመዝገብ
ጓጉተዋል፡፡ የቀሩትም ጠጋ እያሉ በሞባይላቸው፣ በአይፓዳቸውና በካሜራቸው ፎቶ ግራፍ ይነሣሉ፡፡ እነዚህ
ምንም ዓይነት ጥያቄ የላቸውም፡፡ እነርሱ የሚፈልጉት የፌስቡክ፣ የኢሜይልና የትዊተር አድራሻ ነው፡፡ እነርሱ
የተጠመዱት ስልክ ለመቀበል ነው፡፡ የእነርሱ ዓላማ ጠጋ ብለው ፎቶ መነሣት ነው፡፡ አባ እንደመሳቅ እያሉ
ያይዋቸው ነበር፡፡
ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገርም፣ መጠየቅም፣ አንዳች መቀበልም፣ አይፈልጉም፡፡ የሚሰጡትም የሚቀበሉትም ነገር
የለም፡፡ የእነርሱ ዓላማ አድራሻና ፎቶ ብቻ ነው፡፡ መጠጋት ብቻ ነው የሚፈልጉት፡፡ መቅረብ አይፈልጉም፡፡
መግባትም አይመኙም፡፡ እነርሱ ለአይፎናቸውና ለአይፖዳቸው፣ ለፌስቡካቸውና ለትዊተራቸው እንጂ ለነፍሳቸው
አልተጨነቁም፡፡ ነገ በፌስቡካቸው ላይ እንዴት አድርገው እንደሚለጥፉት ነው የሚያስቡት፡፡ ስንት ሰው ‹ላይክ› እና ‹ሼር› እንደሚያደርጋቸው ነው የሚታሰባቸው፡፡ ዓላማቸው እንደ ፈያታዊ ዘየማን ቀድመው ገነት መግባት
ሳይሆን ቀድመው ፌስ ቡክ ላይ መለጠፍ ነው፡፡እነርሱ የእግዚአብሔርን ፎቶውን እንጂ መንግሥቱን አልፈለጉም፡፡
ቀስ በቀስ ሁሉም ከአካባቢው ጠፉ፡፡ አንድ የገረመው ሰውም የተከፈተ ላፕቶፕ ይዞ ወደ አባ ዘንድ መጣ፡፡
‹‹ምንድን ነው?›› አሉ አባ፡፡ ፌስቡኩ ሁሉ በፎቶ ግራፍ ተጥለቅልቋል፡፡ ብዙዎች ዋናውን የፌስ ቡክ ፎቷቸውን
ቀይረውታል፡፡ ፎቶዎችንም ብዙ ሰው ‹ላይክ›4እና ‹ሼር›4አድርጓቸዋል፡፡
‹አዩ አይደለም አባ› አላቸው ፈጣሪ፡፡ ‹‹የዛሬ ሁለት ሺ ዓመት እንደተገለጥኩት ሆኜ ዛሬ ብገለጥ ኖሮ አራቱ
ወንጌሎች በብሎግ፣ የየዕለቱ ትምህርት በትዊተር ነበር የሚወጣው፡፡ አምስት ገበያ ሰው እኔን መከተል ትቶ
አምስት ሺ ሰው በፌስ ቡክ ላይክ ያደርግ ነበር፤ እነ ጴጥሮስም ሲሳሳቱ አልቅሰው ንስሐ አይገቡም ነበር፤ ዲሊት
ያደርጉት ነበር እንጂ፤ ፈሪሳያንንና ሰዱቃውያንን የሚከራከራቸው ሳይሆነ ‹አን-ላይክ› የሚያደርጋቸው ይበዛ ነበር፡፡
አዳምን ለማዳን ብዬ ቅድስት ነፍሴን ከቅዱስ ሥጋዬ ስለይ እንደ ቅድስት ድንግል ማርያምና እንደ ቅዱስ ዮሐንስ
የሚያለቅስ ሳይሆን ፌስ ቡኩ ላይ ‹R I P› የሚል ይበዛ ነበር፡፡
ሐዋርያትም ወንጌልን ሲያስተምሩ እንደ አይሁድ የሚወግራቸው እንደ ኔሮን የሚሰይፋቸው አይኖርም፡፡ በፌስ
ቡክ የሚሰድባቸው፣ ‹አን-ፍሬንድ› የሚያደርጋቸው፤ ሥዕላቸውን አጣምሞ በፎቶ ሾፕ እየሠራ የሚዘብትባቸው፤
‹የእገሌ ደጋፊ ስለሆናችሁ ነው፣ የእገሌ ተቃዋሚ ስለሆናችሁ ነው› የሚላቸው ይበዛ ነበር፡፡ ዛሬ ሰማዕትነት
በሰይፍና በድንጋይ ሳይሆና በብሎግ፣ በትዊተርና በፌስቡክ ነው፡፡
ጲላጦስ አሳልፎ ሰጥቶኝ አይሁድ ሲገርፉኝ የሚያሳየው ሥዕል በፌስ ቡክ ሲወጣ ደግሞ ትውልዱ በሙሉ ‹ላይክ›
ያደርግ ነበር፡፡ በሦስተኛው ቀን ስነሣ ደግሞ ‹ሼር›ያደርጋል፡፡ አዩ አባ ዛሬኮ የሰውን ሃሳብና ችግር ሼር የሚያደርግ
የለም፤ የሰው ፎቶ ግን ብዙዎቹ ሼር ያደርጋሉ፡፡ ዛሬኮ ሰው ሞተ ሲባል ከማዘን ይልቅ ‹ላይክ› እና ‹ሼር› ነው
የሚደረገው፡፡ ታድያ በዚህ ዘመን ለምን ተገለጥ ይሉኛል? በዚህ ዘመንኮ የሁሉም ነገር ዋጋ ከ‹ላይክ›ና ከ‹ሼር›
አይበልጥም፡፡ ዛሬ እኔን ‹የሚወደኝ›4ሰው ነፍሱን ለወገኑ አሳልፎ በመስጠት አይደለም ፍቅሩን የሚገልጠው፡፡ ‹እኔ
ጌታን እወደዋለሁ፤ እናንተስ?› እያለ ‹ላይክ›ና ‹ሼር› አድራጊ በማብዛት ነው፡፡ ወደፊት ደግሞ ጾምና ጸሎት
በፌስቡክ ይሆናል፡፡ ቅዳሴ ማስቀደስም ‹ላይክ›ና ‹ሼር› በማድረግ ይገለጣል፡፡ እና በዚህ ዘመን ለምን ተገለጥ
ይሉኛል? ዋጋው ከ‹ላይክ› ና ከ‹ሼር›4ላያልፍ፡፡››አላቸው፡፡
አባ ከእንቅልፋቸው ነቁ፡፡
Pages: 1