ሄሎ ሀበሻ ምርጥ የሀበሻ መዝናኛ ሰፈር፣
ይህ ዌብ ሳይት ሀበሻን ከመላው አለም በማገናኘት የሚያወያይ
የሚያዝናና ዌብ ሳይት ወይም መድረክ ነው፥፥
ተሳተፉ ፣ ኮመንት አድርጉ ፣ የራሳችሁን ፃፉ
0 users browsing Government. | 1 guest
Pages: 1
Posted on 07-31-16, 10:22 pm


Karma: 90
Posts: 85/879
Since: 02-29-16

Last post: 34 days
Last view: 34 days
አለም አቀፍ እውቅና ያገኙ የመጀመሪያዋ ሴት አፍሪካዊ መሪ ንግስት ዘውዲቱ ፤

================
ዘውዲቱ ከአባቷ ከአፄ ምኒልክ እና ከእናቷ ከወይዘሮ አብችው በእነዋሪ ከተማ ጅሩ ሚያዝያ 22 ቀን 1868 ዓ.ም ተወለደች። እድሜዋም ስድስት ዓመት ከመንፈቅ ሲሆን ያስራ ሁለት ዓመት ዕድሜ ላለው ለአፄ ዮሐንስ ልጅ ለራስ አርአያ ሥላሴ ተዳረች። ይህም የሆነበት ምክንያት በጽዮኑ መንበር በተቀመጠው አፄ ዮሐንስና በይሁዳ አንበሳ ስርወ መንግስት መንበር ላይ ለመቀመጥ በሚጠባበቁት ዳግማዊ ምኒልክ መካከል መግባባትን ለመፍጠር ተብሎ እንደነበር ይነገራል። ራስ አርአያ ስላሤም ከዚህ አለም በሞት ሲለይ የአዲስ አበባውን ፊታውራሪ ውቤ አጥናፍ ሰገድን አግብታ አራዳ ባለው አሁን ደጃች ውቤ ቤት ወይም የአዲስ አበባ የባህል ምግብ ቤት የሚባለው ቤት ውስጥ ትኖር ነበር። ሆኖም አንድ ቀን ወይዘሮ ዘውዲቱ ፊታውራሪ ውቤ በጥፊ ሲመቷት ተናድዳ በማግስቱ ጧት ጠፍታ ሄዳ ላባቷ ለአፄ ምንሊክ ትናገራለች። አፄ ምኒልክም ፊታውራሪ ውቤን አስጠርተው "ምነው መታ ኸኝ " ብለው ጠየቁዋቸው።
ፊታውራሪም ደንግጠው መልስ ባያገኙም አፄ ምኒልክ በትልቁ እጃቸው በጥፊ ብለው ወደቤታቸው ላኩዋቸው። ወይዘሮ ዘውዲቱም ወደቤቷ መመለስ ስላልፈለገች ተፋቱ። ዘውዲቱ ቀጥሎም የጎንደር ገዥና የእቴጌ ጣይቱን የወንድም ልጅ ራስ ጉግሣ ወሌን አገባች ። አብረውም አሁን አዲስ አበባ ፣ ዑራ ኤል ቤተክርስትያን አካባቢ ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጤና ጥበቃ ቢ ሮ ያለበት ቦታ ላይ ይኖሩ እንደነበር ይነገራል ።
ዘውዲቱ ከሦስቱም ባሎችዋ ልጅ አልወለደችም። አባትዋ አፄ ምኒልክ እንደታመሙ እርሳቸውን ለማስታመም ቤተ መንግስት መጥታ አብራቸው መኖር ጀመረች። ዓጼ ምኒልክ ታህሳስ 3 1906 ዓ.ም ቢሞቱም የመሞታቸው ሁኔታ ይፋ ስላልሆነ ቤተ መንግስት ውስጥ ቆይታ የአፄ ምኒልክ የልጅ ልጅ አቤቶ ኢያሱ በጥር ወር 1908 ዓ.ም እቴጌ ጣይቱን ከቤተ መንግስት በግዞት ወደ እንጦጦ ሲልካቸው እሷንም ርስቷ ወደ አለበት ወደ ሸዋ ፉሌ ላካት።
አቤቶ ኢያሱን ከመንግስት ስልጣን ለማውረድ በመኩዋንንቱ በኩል ስምምነት ቢደረስም እርምጃ ለመውሰድ ህዝቡ የእምየ ምኒልክ ተዋላጅ ከሥልጣን መውረዱን ይቃወማል ተብሎ ስለተፈራ ወይዘሮ ዘውዲቱ ንግስተ ነግስት እንዲሆኑ ታጩ። ሹመቱንም ተቀብለው በ43 አመት እድሜያቸው ዙፋን ላይ ተቀመጡ። ንግስተ ነግስት ዘውዲቱ መንፈሳዊነታቸውን የሚያጠብቁ ስለሆኑ ባለቤታቸውን ራስ ጉግሣ ወሌን ትተው በብትህና ለመኖር መርጠዋል ተባለ። ራስ ጉግሣም ጎንደር እንደገና ተሹመው ከቤተ መንግስት እንዲርቁ ተደረገ። ደጃች ተፈሪ መኮን (በሁዋላአፄ ኃይለ ሥላሴ) ራስ ተብለው እና አልጋ ወራሽ ሆነው ተሾሙ።
ፖለቲካውን ለመምራትም ሆነ ዘመናዊ ሥልጣኔን ለማስፋፋት ተፈሪ ለሚያደርጉት ጥረት ሁሉ ንግሥት ዘውዲቱ እንቅፋት አልሆኑም። ይልቁንም በበኩላቸው ቤተ ክርስትያን ሲያሰሩና ሲያሳድሱ ፣ በተጨማሪም የቅዱስ ጊዮርጊስ ትምህርት ቤትንና የንግስት ዘውዲቱ ማዋለጃ ሆስፒታልን ማሰራት ላይ ትኩረታቸውን አደረጉ። የሚከተሉትም ካሰሩዋቸው ቤተክርስትያኖች ውስጥ ይጠቀሳሉ።
--
አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ
ቅዱስ ዑራኤል
የታዕካ ነግሥት ባዕታ ለማርያም
ጴጥሮስ ወጳውሎስ
ደብረ አሚን ተክለ ሃይማኖት
ቅዱስ ዮሴፍ ወኒቆዲሞስ
ደብረ ነግስት ቁስቇም
ከአዲስ አበባ ውጭ የሚገኙ
ፉሌ መድኃኔአለም
መናገሻ ማርያም
የረር ቅድስት ሥላሴ
ጀርሳለፎ ቅዱስ ገብርኤል
አዋሽ ቅድስት ማርያም
አድአዘርጋ አቡነ ተክለኃይማኖት
--
ሜታ የወረብ ቅድስት ማርያምንስግስት ዘውዲቱ አባታቸው አፄ ምኒልክ የምእራባውያንን ስልጣኔ ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት የነበራቸውን ፍላጎት በሚገባ የተገነዘቡ ስለነበሩ በበኩላቸው ትምህርት እንዲስፋፋ አዋጅ አወጡ። አዋጁም እድሜው ከ7 እስከ 21 አመት ድረስ የሆነ ልጅ ያለው 1ኛ) የንባብና የፅሕፈት ትምህርት ፣ 2ኛ) በአገራቸን ካለው የእጅ ሥራ ውስጥ ልቡ የወደደውን ለልጁ እንዲያስተምር የሚደነግግ ነበር። ካላስተማረ ግን 50 ብር ቅጣት እንዲቀጣ የሚልም ነበር። ይህንንም የመቆጣጠሩ ሃላፊነት የንሥሐ አባት ፣ የገጠር መሪጌታ እና የደብር አለቃ ሁሉ ግዴታ ተጥሎባቸው ነበር።
ንግስቲቱ ስልጣኔን ልጠቀም ብለው ሳያስቸግሩ ለ12 አመት ከግማሽ አልጋው ላይ ቢቀመጡም አልጋ ወራሹ ራስ ተፈሪ የንግስት ዘውዲቱን ደጋፊዎች በማግለልና የራሳቸውን ደጋፊዎች በየቦታው በመሾም ኃይላቸውን አጠናክረው የመንግስቱን ስልጣን ለመውሰድ እየተዘጋጁ ይሄዱ ጀመር። ተፈሪንም ለማንገስ ውስጥ ውስጡን በደጋፊዎቻቸው ሢጠነሰስ ከቆየ በሁዋላ ቀኝ አዝማች ባንትይዋሉና ግራዝማች ይገዙ የሚመሩት ቡድን ንግስተ ነገስት ዘውዲቱን "ራስ ተፈሪን ያንግሱልን" ብለው ሲጠይቁ "እስቲ ልዋል ልደርና መክሬ መልሱን እሠጣችሁዋለሁ" ሲሉ ቢመልሱላቸውም "አይሆንም አሁኑኑ መልሱን ካልሰጡን" ብለው ሰቅዘው ያዙዋቸው። ንግስተ ነግስትም ነገሩ ስለገባቸው የነበራቸው አማራጭ መስማማት ብቻ ነበርና ተስማሙ። ስለሆነም ራስ ተፈሪ ንጉስ ተፈሪ ተብለው መስከረም 27 ቀን 1921 ዓ.ም ዘውድ ደፉ።
ከዚህ ሹመት በሁዋላ ግብር በሁለት ቦታ እየተበላ ሰው እየተከፈለ በንግስቲቱና አዲሱ ንጉስ መካከል ውስጥ ውስጡን አለመግባባት እየፈጠረ ሄደ። ቅሬታ አሳይተው የነበሩትን የንግስቲቱን የበፊት ባልና የጎንደሩን ገዢ ራስ ጉግሣ ወሌንም ማስወገድ አስፈላጊ ሆነ። ራስ ጉግሣ ወሌም ወደ አዲስ አበባ ሲጠሩ አኩርፈው ለመምጣት ባለመቻላቸው በነደጃች ሙሉጌታ የሚመራ ጦር ዘመተባቸው። በዚሁም ውጊያ አንቺም ላይ ራሳቸውን በጎራዴ ተመተው ተገደሉ። ንግስት ዘውዲቱም ከራስ ጉግሳ ወሌ ሞት በሁዋላ በሁለተኛው ቀን መጋቢት 24 ቀን 1922 ዓ.ም ከዚህ አለም በሞት ተለዩ። ንግስቱዋ በዚህ ወቅት በስኩዋርና በታይፎይድ በሽታ ይሰቃዩ ነበር ፤፤ ንግስተ ነግስት ልጅ ስላልነበራቸው መሬታቸውንና ንብረታቸውን ልዕልት ተናኘ ወርቅ እንዲወርሱ ተደረገ ።የአባታቸውን ሃውልት ሳይመርቁ፣ አረፉ፡፡ ሲሞቱ የቀድሞ ባላቸውን የራስ ጉግሳን በጦርነቱ ላይ መሞት አልሰሙም ነበር ይባላል፡፡ ንግስት ነገስታት ዘውዲቱ በማግስቱ በታላቅ ክብር በይፋ የቀብራቸው ስነ-ስርዓት ተፈፀመ፡፡ በኢትዮጵያ የነገስታት ታሪክ ከዘመነ መሳፍንት ወዲህ፣ በይፋና በክብር ለመቀበር ንግስት ዘውዲቱ የመጀመሪያዋ መሪ ናቸው፡፡
--
ምንጭ :
የ20ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ፣ በጥላሁን ብርሃነ ሥላሴ
የኢትዮጵያ ረጅም የህዝብና የመንግስት ታሪክ ፣ በዶክተር ላጵሶ ጌ. ድሌቦ "
Source: Henze, Paul B. (2000). Layers of Time, A History of Ethiopia. New York: Palgrave
Bahru Zewde (2001). A History of Modern Ethiopia (second ed.). Oxford: James Currey.
Pages: 1