ሄሎ ሀበሻ ምርጥ የሀበሻ መዝናኛ ሰፈር፣
ይህ ዌብ ሳይት ሀበሻን ከመላው አለም በማገናኘት የሚያወያይ
የሚያዝናና ዌብ ሳይት ወይም መድረክ ነው፥፥
ተሳተፉ ፣ ኮመንት አድርጉ ፣ የራሳችሁን ፃፉ
0 users browsing Religion. | 1 guest
Pages: 1
Posted on 07-25-16, 08:44 pm


Karma: 100
Posts: 137/444
Since: 07-20-15

Last post: 73 days
Last view: 73 days
የብራና ጽሑፍ በኢትዮጵያ ፤
ከስሜነህ ጌታነህ Diretube
----
ላለፉት በርካታ ዘመናት ኢትዮጵያን በተዋቡ የቅብ ሥዕሎች፣ የተጌጡና በደንብ የተጠረዙ የብራና ፅሁፎች በማዘጋጀት ጥበብና የላቀ ችሎታ ነበራቸው። በመጀመሪያ ድንጋይ፣ ሸክላ፣ እንጨት፣ ብረትና ሌሎችንም መሠል ነገሮች እየተፈለፈሉ የእለት ተዕለት ሃሣቦችና ሁኔታዎችን የመመዝገቡ ዘዴ ከፍተኛ እድገት አሣየና በተለይ በኢትዮጵያ ብቻ የሚሠራበት አይነት የብራና ጽሑፍ ሊተካ ችሏል።
ብራና ኢትዮጵያ ውስጥ ለጽሕፈት ከዋሉት ጥንታዊ ነገሮች መካከል አንዱ ሲሆን፣ በአገልግሎት ላይ መቼ እንደዋለ ግን በውልና በግልጽ አይታወቅም፡፡ ሆኖም በጥንት ጊዜ በአክሱም ዘመነ መንግሥት የብራና ጽሑፍ ዋና ሆኖ ያገለግል እንደነበረ የሚታመን ነው፡፡ ነገር ግን በብራና ላይ መጻፍ በሰፊውው የተለመደውና በሥራ ላይ የዋለው የክርስትና ሃይማኖት ከገባ በኋላ በአራተኛው ምዕት ዓመት በአብርሃ ወአጽብሓ ዘመነ መንግሥት ነው፡፡ ብራና ከሌሎች ሊመረጥ የቻለው ምናልባት ለስላሳ፣ የማያስቸግርና ቀላል በመሆኑና እንዲሁም በአገሪቱ በርኮታ የቤት እንስሳት ስለነበሩና ጥሬ ሀብቱ በብዛት በመገኘቱ ቆዳው በሚገባ ከተፋቀ በኋላ ለጽሕፈት መሣሪያነት እንዲያገለግል ተደረገ ፡፡
ብራና ከለማዳ እንስሳት ቆዳ እንደ በሬ ፣ ላም ፣ ጥጃ ፣ ፍየል ፣ በግና ፈረስ እንዲሁም ከዱር እንስሳት ቆዳ እንደ አንበሳ፣ ነብር ፣ የሜዳ ፍየልና ድኩላ ከመሳሰሉት የተለያዩ እንስሳት ሊዘጋጅ ይችላል፡፡ የፍየል፣ የበግ፣ የጥጃ፣ የፈረስ፣ የሜዳ ፍየልና የድኩላ ቆዳዎች ከሌሎች የተሻሉ ሲሆኑ በነጭነታቸውና በቀለም ተቀባይነታቸው ደግሞ የፍየልና የሜዳ ፍየል ቆዳዎች በይበልጥ ይመረጣሉ፡፡ የፍየል ቆዳ በተለይ ለስላሳና ጠንካራ በመሆኑ ከፍየል ቆዳ የተሠሩ ብራናዎች እጅግ ተፈላጊ ሆኑ ፡፡ ስለዚህ ብዙዎቹ ዋና ዋና የብራና ጸሑፎች የተዘጋጁት ከፍየል ቆዳ ነው። ስለሆነም የመጻፍ ችሎታ ያላቸው መነኮሳት ደባትሮች በየገዳማቸው፣ በየደብራቸውና በየቤታቸው ሆነው የፍየልን ቆዳ ፍቀውና እለዝበው ብራናውን ልክ እንደዛሬ ዘመን ወረቀት ዓይነት አስመስለው በመቃና በቀጫጭን ሸምበቆዎች ብርዕ እንዲጻፍበት አድርገው ያዘጋጁታል ፡፡
በድሮ ዘመን በብዛት የሚጻፉ መንፈሳዊያን መጻሕፍት ስለሆኑ እነርሱም ከቅዱሳት መጻሕፍት ብሉይና ሐዲስ፣ ከአዋልድ መጻሕፍት ሊቃውንትና መጻሕፍተ መነኮሳት ፥ ገድል፣ ድርሳን ተአምር የተባሉት ሲሆኑ፤ ቅዱስ ያሬድ ከደረሳቸው ከዜማ መጻሕፍትም በዓለም የታወቁ ድጓ፣ ጾመድጓ፣ ምዕራፍ፣ ዝማሬ መዋሥዕት የተባሉት ናቸው። ሌሎችም እንደ ፍትሐ ነገሥት፣ ታሪከ ነገሥትና ክብረ ነገሥት የመሳሰሉ የተከበሩ መጻሕፍት ይገኙባቸዋል ፡፡ ከነዚህም በቀር ስለ ኢትዮጵያ ባሕላዊ ሕከምና፣ የአባቶችን ወግንና ሥርዓትን የሚገልጹ መጻሕፍትም እንዳሉ አይዘነጋም። እንግዲያውስ ኢትዮጵያ አሉኝ ብላ ከምትመካባቸው ቅርሶች አንዱ የብራና መጻሕፍት ናቸው፡፡ ምክንያቱም የያዙት የታሪክም ሆነ የወግና ሥርዓት ትምህርቱ በጣም ጠቃሚ ስለሆነ ነው ፡፡ ብራናው በጸሐፊው መኖሪያ ቤት የአጥር ግቢ ውስጥ እንደሚከተለው ሊዘጋጅ ይችላል፡፡
በመጀመሪያ ደረቁም ሆነ እርጥቡ የፍየል ቆዳ ይሰበሰባል ፤
ከዚያም በኋላ በውኃ ይዘፈዘፋል ቀጥሎም ከውኃ ወጥቶ በጠፍር መወጠሪያ ወይም ገመድ አራት ማዕዘን ባለው ቀምበር ላይ ይወጠራል፤
ከዚያም የቆዳው ልፋጭ በቆልማማ ቢላዋ ይገፈፋል፤
ቀጥሎም የተደቆሰ ጨው እየተነሰነሰበትና ውኃም እንደ አስፈላጊነቱ እየተርከፈከፈበት በመራመሚያ ድንጋይ እየተራመመ ከልፋጩ ሁሉ ንጹሕ ይሆናል፡፡
ቀጥሎም እንዲደርቅ ይደረግና በተዘጋጀው ምሳር ተፍቆ እንደገና ጨው ተደርጎበት ይራመምና ከዚያ በኋላ ይደርቃል፡፡
ቀጥሎም የደረቀው ብራና በአስፈላጊው መጠን እየተለካ ጥራዞች እንዲያገኝ ተደርጎ በመቀስ ይቆራረጣል፤
ቀጥሎም ጥራዞቹ መስመር እንዲኖራቸው በማስመሪያና በወስፌ እየተሰመሩ መስመር ይዘጋጅላቸዋል፤
ከዚህም በኋላ በመዳመጫ እየለዘበ የቁም ጽሕፈቱን መጻፍ ይቀጥላል ፡፡
በአብዛኛው ለጠቀሜታ የሚውሉት ጥቁርና ቀይ ቀለም ዓይነቶች ሲሆኑ፣ ሁለቱም ለተለያዩ ዓላማ ያገለግላሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ጸሐፊዎች ጥቁር ቀለም ከቅጠል፣ ከከሰል፣ ከምጣድ ጀርባ፣ ከሚራገፉ ጥላሸቶችና ጥቀርሻዎች፣ ቀይ ድንጋይ፣ በርበሬ ያዘጋጃሉ። ለሥዕል ደግሞ የእንቁላል አስኳል፣ ቀይ አፈርና ሙጫ ከመሳሰሉ በመሰብስብና ተቆልቶ አንዲያር ከተደረገ እህል (ሐሩር) ጋር ቀላቅለው በመለወስና በማብኳት እንደ አስፈላጊነቱ ቀይ ወይም ጥቁር ቀለም እንደሚከተለው አዘጋጅተው ይጠቀማሉ፡፡
እንደተፈለገው የቀለም አይነት ከላይ የተጠቀሡትን ነገሮች ተቀላቅለው ማሰሮ ውስጥ ከከተቱት በሇላ እሥኪብላላ ድረስ በየጊዜው እየታሸ ለበርካታ ቀናት ይቆያል።
ከነኝህ የቀለም ቅመሞች ሌላ የደረቀ አበባና ስራስርም ከሙጫ ጋር ቀላቅለው ቀለም በማዘጋጀት ጥቅም ላይ ያውሉት ነበር። የተቀመሙት ነገሮች ተወቅጠውና ተደቁሠው እየታሹ ይቆያሉ።

ቀለሙ እየቦካ ሲሄድም የማጣበቅ ጠባይ ይሮረዋል። ከዚያም በንፁህ ጨርቅ ይጠለላል። ብራናውን ማዘጋጀቱ በቂ ዕውቀት እንደሚጠይቀው ሁሉ ቀለም መቀመሙም ዕውቀትን፣ ችሎታንና ትዕግሥትን የሚጠይቅ ሥራ ነው፡፡

በመጨረሻ ጥቁሩ ቀለም በጥቁር ቀንድ፣ ቀዩ ቀለም ደግሞ በቀይ ቀንድ ይቀመጣል፡፡
ጥንታዊያን ጸሐፊዎች ሸምበቆንና የመቃ ብርዕን እንዲሁም የትልልቅ አሞሮችና ንስሮች ላባን እንደ ብዕር አድርገው ይጠቀሙባቸው ነበር፡፡ ሽምበቆውን ወይም መቃውን እንደሚፈለገው ዓይነት መካከሉን ሰንጠቅ አድርጎ ይቀርፀዋል፡፡ የመጽሐፉ ርዕሶችና የቅዱሳን ስሞች የእግዚአብሔር ፥ የኢየሱስ ክርስቶስ ፡ የማርያም ፥ የመላፅክትና ወዘተ በቀይ ቀለም ይጻፋሉ፡፡ ይህ የአጻጻፍ ዘዴ በየዐረፍተ ነገሮች መሐክልም አልፎ አልፎ ይደረጋል፡፡ መጻሕፍቱም በጉልህ ጥቁርና ቀይ ቀለም በመስቀለኛ ነቁጥ በሥዕል ሐረጎች ያጌጡ ናቸው።
ብራናዎቹ በሚጸፍባቸው ጊዜያት ግማሹ ወይም ሙሉው ገጽ ለሚያስፈልገው ሥዕል ክፍት ሆኖ ይቀራል፡፡ ሥዕሎቼ የሚቀቡት ተመልካቹን በሚማርኩ ዓይነት ውብ የኅብር ቀለማት ነው፡፡ የገጾቹም ጠርዞች አንዳንድ ጊዜ በተለያዩ ኅብሮች የተጌጡ ናቸው ፡፡ መስቀሎች፣ ቅጠሎችና ጂኦሜትሪን የተከተሉ ቅርጾች በተናጠል ወይም በተለያየ መንገድ ተዳምረው ይታያሉ ፡፡ ከዚያም በመጀመሪያ የብራና ቅጠሎች ጸሐፊው በፈለገው መጠን ጥራዞቹን ይወስናል፡፡ ከተጠረዘም በኋላ ተደጉሶ አንድ መጽሐፍ ይሆናል፡፡
የብራና መጽሐፍ ሲባል በውስጡ አንድ ዓይነት ሐሳብ ወይም የተለያዩ ሐሳቦችን አካትቶ ሊይዝ ይችላል ፡፡ ታላላቆቹ እንደ ወንጌል ፡ እንደ ግብረ ሕማማት ፥ እንደ ስንክሳር ያሉት ገበታቸው በወርቅ ወይም በብር ሊለበጥ ይችላል፡፡ ጻሐፊዎቹ ማንኛውም ዓይነት ጽሑፍ ለመጻፍ ሲጀምሩ "በስመአብ ወወልድ ወወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ንዊጥን በረድኤተ እግዚአብሔር ጽሒፈ ገድለ ... ጽሒፈ ድርሳነ ... ጽሒፈ ዜናሁ ለእገሌ ... ጽሒፈ ዜና ታሪክ ዘኢትዮፕያ" በማለት ረድኤት እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ መጻፍ ይጀምራሉ፡፡ ይህን የመሳሰለውን መቅድመ ጽሑፍ አብዛኛውን ጊዜ የሚጽፉት በቀይ ቀለም ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ የአመቤታችንን፣ የጻድቃንን የሰማዕታትን፣ የሐዋርያትንና የእግዚአብሔርን ስም በቀይ ቀለም ይጽፋሉ፡፡ ለምዕራፍ መክፈያ ለነጥቦች ማሰራጫ ለሐረግ መጣያ በቀይ ቀለም ያጠቀማሉ።
ከነኝህ ወደርየለሽ የብራና መጻሕፍት አብዛኛዎቹ በዮዲትና በግራኝ አሕመድ እንዲሁም በደርቡሾች ጦርነት ጊዜ ተቃጥለዋል። የቀሩትም ተዘርፈዋል ፡፡ በኢጣሊያ ፋሺስቶች ወረራና በእንግሊዞችም ተወስደዋል ፡፡ ከዚህም የተረፉ ታሪክ አቀፍ የብራና መጻሕፍት በኦውሮፓውያን ሚሲዮናዊያን ተጓዦችና ሀገር አሳሾች በየጊዜው ተመዝብረዋል። በእንግሊዝ ሀገር ብቻ 700 ያህል የተለያዩ የብራና መጻሕፍት በየሙዚየምና በየቤተ መጻሕፍቱ ይገኛሉ፡፡ አጼ ቴዎድሮስ አንድ ሺ ያህል የብራና መጻሕፍት መቅደላ ላይ ሰብስበው እንደ ነበረና ከነኝህም አብዛኛዎቹ በእንግሊዝ ሠራዊት ተዘርፈው ስለተወሰዱ ከነሱም ውስጥ ከብረ ነገሥት የተባለው የታሪክ መጽሐፍ ብቻ በአጼ ዮሐንስ አራተኛ ጥያቄ ሊመለሰ ችሏል ፡፡
ዛሬ ዋና ዋናዎቹ የብራና ጽሔፎች በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት በአክሱም ጽዮን ማርያም, በደብረ ዳሞ ፡ በጉንዳጉንዴ፣ በሚካኤል አምባ፣ በቤተልሔም፣ በደብረ ቢዘንና ደብረሊባኖስ፣ በጣና ሐይቅ ደሴቶች ላይ በሚገኙ ገዳማት እንዲሁም በጎንደር፣ በጕጃምና በወሎ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት ነው። በውጭ ሀገርም የኢትዮጵያ የብራና መጻሕፍት በፓሪስ፣ በቫቲካን ፥ በሞስኮና በበርሊን ከተማዎች ቤተ መጻሕፍት በብዛት ይገኛሉ፡፡ እነዚህም የብራና ጽሑፎች በይበልጥ ተደናቂ የሚያደርጋቸው ከብራና አዘገጃጀቱ ጀምሮ እስከ ቀለሙና የብርዕ አቀራረጹ ድረስ በኢትዮጵያውያን ሊቃውንት እየተዘጋጁ የተጻፉ በመሆናቸው ነው፡፡
Posted on 09-12-16, 06:38 am
Red Paragoomba


Karma: 100
Posts: 25/50
Since: 08-22-16

Last post: 965 days
Last view: 950 days
(የኔ ሃሳብ) ፥ ለምን ሃገራችንን ጠላት እንደበዛባት አብዛኛው ሚስጥር ቢሆንብኝም ነገር ግን ያ ሁሉ ጠፍቶ እንኳን አሁንም የአባቶች ታሪክ ጎልቶ ይታያል። ለማንኛውም ለታሪክ ሰሪዎቻችን ክብርና ምስጋና ይድረሳቸው። እኛም በዘመናችን በየሙያችን ለሃገሬ የሚል ቀሪ ስራ ሊኖረን ይገባል።
_________________________
አመሰግናለሁ።
Pages: 1