ሄሎ ሀበሻ ምርጥ የሀበሻ መዝናኛ ሰፈር፣
ይህ ዌብ ሳይት ሀበሻን ከመላው አለም በማገናኘት የሚያወያይ
የሚያዝናና ዌብ ሳይት ወይም መድረክ ነው፥፥
ተሳተፉ ፣ ኮመንት አድርጉ ፣ የራሳችሁን ፃፉ
0 users browsing Education - ትምህርት. | 1 guest
Pages: 1
Posted on 07-23-16, 05:22 pm


Karma: 90
Posts: 71/887
Since: 02-29-16

Last post: 129 days
Last view: 129 days
ውጊያውን ብታሸንፉም ጦርነቱ ገና ነው!
(ካሳዬ ሰን'አን)

ይድረስ ለእናንተው ላልረገፋችሁት የዘንድሮው የግንቦት ሀያ ፍሬዎች። በረገፉት ጦሰኛ የ12ተኛ ክፍል ተፈታኞች ሰበብ የደስታችሁን ፎቶዎች ወዲያውኑ በመለጠፍ ፌስቡክን ባለመሙላታችሁ እንዳዘናችሁ ይገባኛል።

ሠሞኑን ከውድቅት ሌሊት የጠቆረ ካባችሁን ተጐናጽፋችሁ፣ ድዳችሁን እያሰጣችሁና በደስታ የተሞላ ፊታቸውን ለጥፋችሁ ስትሽከረከሩ የምናያችሁ የዘንድሮ ተመራቂዎች፤ እጣ ፈንታችሁ እያሳሰበን ነው። ጠረጴዛ የመሰለውን ባርኔጣ መሀል አናታችሁ ላይ ከወሸቃችሁ፤ ዓለምን በእጃችሁ የጨበጣችኋት፣ ስኬት መሰላል አናት ላይ የተንጠላጠላችሁ፣ ዳር የወጣችሁ፣ ቀን የወጣላችሁ መስሏችሁ ደረታቸውን በኩራት ለነፋችሁት፤ ለእናንተው።

ምንአልባትም አኔም በእናንተ ቦታ እያለሁ ከዚህ የተለየ ስሜት እንዳልነበረኝ እጠራጠራለሁ። ሆኖም እኔ በእናንተ ቦታ እያለሁ ጮቤ መርገጤን ቀንሼ ስለሚጠብቀኝ ከባድ ፍልሚያ በትንሹ እንኳ ባስብ አሊያም በእኔ ጫማ ያለፈ ቢገስጸኝ፤ ጦርነቱ ሲጧጧፍና ፈተናው ሲከብድ፤ ተስፋዬ፣ ምኞቴ፣ እምነቴ፣ በራስ መተማመኔ ተንኮሻኩሾ አይወድቅም ነበር። እናም ራሳችሁን አዘጋጅታችሁ ወደ ገሀዱ ዓለም እንድትወጡ ምክሬን መለገስ አስፈላጊ መስሎ ታይቶኛል። ዛሬ እኔ የምነግራችሁን አስፈላጊ ነጥቦች፤ ለእኔ ተነግረውኝ ቢሆን ኖሮ ብዙ ነገሮች ይለወጡ ነበር።

ሥራ ፍለጋ እንደ መመረቂያ ጽሁፋቸው ብዙ ቦታ ማሰስን፣ መማሰንን፣ ሠፊ ጊዜን፣ መጠያየቅን፣መለማመጥን፣ የሠው ፊት ማየትን እና ትዕግስትን ይጠይቃል (በተለይም በሀገራችን)። ጥሩ ውጤትም ላይገኝበት ይችላል። ዘው ብላችሁ የምትገቡበት አይደለም። እንደየ ትምህርት ዘርፋችሁ፤ ሦስትም፣ አራትም፣ አምስትም ዓመታችሁን ጠጥታችሁ ፤ ሥራ ለማግኘት አገር ምድሩን እንደ ማጅላንድ ስታስሱ ያለውን ድካምና መሰናክልን እንደ ሁለተኛ ድግሪያች ብትቆጥሩት ሳይሻል አይቀርም። አታስፈራሪን አትበሉኝ። አይ “ስራ ፈላጊ” አንሆንም ካላችሁኝ ምንአልባትም ከዩኒቨርስቲው በተጨማሪ መንግስት ከመሰሎቻችሁ ጋር አደራጅቶ “ስራ ፈጣሪ” እንድትሆኑ ይመርቃችሁ ይሆናል። ምን ይታወቃል የሱ ሥራ። አይዟችሁ ኢንጅነሮች ከሆናችሁ እናንተ ከወዲሁ “ስራ ፈጣሪ” መሆናችሁ ስለተባነነ “መስሪያ ፈቃዳችሁን” ለቻይናዊያን ታከራያላችሁ። ይህም ስራ ነው። አይደል እንዴ?
በአጭሩ በዚህ ዘመን የድግሪን ብጣሽ ወረቀት ይዞ ስራ ማግኘት ከባድ ነው። እንዴት አላችሁኝ? ጥሩ፤ አንዳንድ መስሪያ ቤቶች በወዳጅ ዘመድ ቀድመው ይቀጥሩና፤ አወዳድረን ቀጠርን ለማለት ብቻ የቅጥር ማስታወቂያ አውጥተው ውድ ጊዜያችሁን ያባክናሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ የአንድ ክበብ (ድርጅት) አባል መሆንን እንደ መስፈርት ቆጥረው ለሥራው ብቁ ያልሆነ ሠው ሥራው ላይ ቁብ ብሎ እንድታገኙትና ከልባችሁ እንድታዝኑ ያደርጋሉ። አንዳንድ የአገራችን እንቁ መስሪያ ቤቶች ደግሞ የግድ ፎር ካላመጣችሁ፤ ካልሰቀላችሁ በስተቀር ዝር እንድትሉባቸው አይፈልጉም። ችሎታችሁን በፈተና እንድታሳዩ እንኳ አይፈቅዱላችሁም። አንዳንዴ ደግሞ ቀንቷችሁ ሥራ ሲወጣ፤ የአንድ መንደር የከብት መንጋ ከሚመስል ከፊሉ ከሚመለከተውና ከማይመለከተው ስራ ፈላጊ ጋር ትፋለማላችሁ። አንገት ለአንገት ትያያዛላችሁ። አብዛኛው የሚጠይቋችሁ ጥያቄዎች እንኳ ከምትፈተኑበት የሥራ ዘርፍ ጋር አይዛመድም።

ይህን ሁሉ የምቀባጥረው ካምፓስ እያላች የህልማችሁን ሥራ እንደምትሠሩ እንዲሁም ስራ በቀላሉ እንደምታገኙ አንዴ ጭንቅላታችሁን በደፈናው አሳምናችሁ ስለምትወጡ፤ ከእውነታው ጋር ስትገጣጠሙ ከራሳችሁ ጋር ጠብ እና ውዝግብ እንደምትጀምሩ ከልምድ ስለማውቅ ነው። ወዳጅ ዘመዶቻችሁም ቢሆኑ ዛሬ በደስታችሁ ደስ ቢላቸውና ቢፍነከነኩ፤ እንደኮሩባችሁ ቢነግሯችሁ፤ ነገ በሥራ እጦትና መንከራተት፤ ምሬትና ሀዘን አፍንጫችሁ እንደሚደርስ አስረግጠው ያውቃሉ። ግን አያስጠነቅቋችሁም። አስራ አምስት፣ አስራ ስድስት. . . ዓመታት የለፋሁት፣ አይኔ እስኪሞጨሙጭና እንደበረዶ እስኪቀልጥ ድረስ ያጠናሁት፣ ቤተሰብስ ለትምህርት ያፈሰሰው መዋዕለ ነዋይ እና ተስፋ ለዚህ ነው? እያላችሁ ከራሳችሁ ጋር ሙግት ትጀምራላችሁ። እምነታችሁ እንደ ልብስ ከገላችሁ ሲወልቅ ይሰማችኋል። የተመረቃችሁ ሳይሆን የተረገማችሁም ሊመስላችሁ ይችላል። የመረቃችሁ ዩኒቨርስቲ ሥራ በሌለበት እንደ ዶሮ ተማሪዎችን በሽህዎች ይፈለፍላል። መጽሄታችሁ ላይ “ወርቅ በእሳት ተፈተነ” ብሎ የጻፈ፤ በአንድ የክብሪት እንጨት ነበልባል ብቻ እንደተፈተነ ሊያውቅ ይገባዋል። ከአስራ አምስት ዓመት በላይ ጭንቅላታችሁን የሞላውን ትምህርት እውቀት፤ እናቱ እንዳልፈለገችው ጨቅላ ህጻን ብታስወርዱት ትመኛላችሁ። የመማርን ከንቱነት ትገነዘባላችሁ። ታወግዙታላችሁም። መማር ከእራሳችሁ አልፎ የመጣችሁበትን ማህበረሰብና ሀገሩን ካለወጠና ካላገለገለ ፋይዳው ምኑ ላይ ነው? እናንተስ ዳር ካልወጣችሁበት ትርጉሙ ምንድን ነው?

እስከመቸውም ጨርሳችሁ አታገኙም ማለቴ አይደለም። ለጥቂት ጊዜያት ሥራ እና እናንተ ሆድና ጀርባ ሆናችሁ ትቀቃራላችሁ። ትንሽ ተስፋ ከቆረጣችሁ በኋላ፤ እምነታችሁ ውሃ ላይ እንደተጣለ ጨው እየሟሟ ሂዶ ጫፍ ላይ ሲደርስ፤ የምኞታችሁንና የከጀላችሁትን ሥራ ባይሆንም ታገኛላችሁ። ለላባችሁ የልፋታችሁን እና የዘመኑን ውድነት ያመዛዘነ ደመ-ወዝ እንደማይከፈላችሁ ግን አስቀድሜ ላረጋግጥላችሁ እፈልጋለሁ። በዚያ የብልጽግና ዘመን (የተማሪነት) በቀላሉ ቤተሰቦቻችሁን እንደፈለጣችሁት፤ መንግስትንም የምትፈልጡት እንዳይመስላችሁ። እሱ ፍንክች አይልምና። ሦስት ሽህ ብር በወር እየተላከለት ቀብጦ የተማረ ስራ ፈላጊ፤ በወር ከወገቡ ሳይጎመድ 2008 ብር (ሲቆራረጥና አዲሱን የታክስ ማሸሻያ ሳይጨምር 1500 ገደማ) ይከፈልሀል ቢሉት ቀልድ ነው የሚመስለው። በእሱስ ትፈርዳላች? ዛሬ ዛሬ የድግሪ ምሩቅ ከቤት ሠራተኛ በታች ነው የሚያገኘው (ሥራ ማናናቄ አይደለም)። ድግሪ ከድግር በትንሽ ቅንጣት እንኳ እንደማይበልጥ ካወቅን ውለን አድረናል።

እናም ውድ ተመራቂዎች፤ በጉጉት ስትጠብቁት የነበረው ገሀዱ “የሥራ አለም” ይኸው ነው። ከአሁኑ ሳይረፍድባችሁ ራሳችሁን አዘጋጁ። ከህይወት ጦርነት አንዷን ምዕራፍ ነው በምርኳዝ ተፋልማችሁና ተዋግታችሁ ያጠናቀቃችሁት። ጦርነቱ ይቀጥላል። ፍጻሜ ያገኘ እንዳይመስላችሁ። መልካም ምኛቴን እየተመኘሁ፤ መልሳችሁን በአፋጣኝ እፈልጋለሁ።
መልካም እድል
Share to ur friends
Pages: 1