ሄሎ ሀበሻ ምርጥ የሀበሻ መዝናኛ ሰፈር፣
ይህ ዌብ ሳይት ሀበሻን ከመላው አለም በማገናኘት የሚያወያይ
የሚያዝናና ዌብ ሳይት ወይም መድረክ ነው፥፥
ተሳተፉ ፣ ኮመንት አድርጉ ፣ የራሳችሁን ፃፉ
0 users browsing Government. | 1 guest
Pages: 1
Posted on 07-03-16, 02:38 am


Karma: 90
Posts: 63/887
Since: 02-29-16

Last post: 206 days
Last view: 206 days
ልባም መንግስት ከመጣ ኢትዮጵያና ኤርትራ በኮንፌደሬሽን ሊተሳሰሩ ይችላሉ
የኢሳያስን መንግስት የማውረድ ኃላፊነት የኤርትራ ህዝብ ብቻ ነው
በድርድር በአሰብም በምፅዋም የመጠቀም መብት አለን
የቀይ ኮከብ ዘመቻ ቢሰምር ኖሮ፣ ይሄን ቃለ ምልልስ ማድረግ ባላስፈለገን ነበር …

የኤርትራ ችግር የሚጀምረው የፌዴሬሽኑ መፍረስን ተከትሎ ነው ይላሉ - በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ላይ ጥልቅ ጥናት ያደረጉት ዕውቁ የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀኝ፡፡ እንዴት? ለአዲስ አድማስ በዝርዝር አብራርተዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በ25ኛ ዓመት የነፃነት በዓላቸው ላይ ባደረጉት ንግግር፤ “ለወርቃማው በዓል ያገናኘን” ማለታቸውን ያስታወሱት ፕሮፌሰሩ፤ ከዚያ በፊት ግን ሁለቱ አገራት በኮንፌደሬሽን ሊተሳሰሩ የሚችሉበት ዕድል ይኖራል” ባይ ናቸው፡፡ የኤርትራን መንግስት በኃይል ስለማውረድ ተጠይቀውም የሶማሊያ አልሻባብና የኤርትራ ብሄራዊ መንግስት ለየቅል ናቸው ብለዋል፡፡ የአሰብና የምፅዋ ወደቦች ያለ ኢትዮጵያ ፋይዳ እንደሌላቸው የታሪክ ምሁሩ ያስረዳሉ፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ ችግር እንዴት ነው የሚፈታው? ምሁሩ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ በፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀኝ መኖሪያ ቤት (ለቡ) ተገኝቶ በኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ ከታሪካዊ ዳራው አንስቶ በስፋት አነጋገሮአቸዋል፡፡

ኤርትራ ከኢትዮጵያ ለመገንጠሏ ታሪካዊ ተጠያቂ የሚሆነው ማን ነው?
ይሄን ለማብራራት የቅኝ አገዛዝንና ኤርትራ እንዴት ነፃ ወጥታ ከኢትዮጵያ ጋር ተዋሃደች የሚለውን ማየት ያስፈልጋል፡፡ ፌደሬሽኑ ለምንና እንዴት ፈረሰ የሚለው ከዚያ በኋላ የሚመጣ ነው፡፡ አፄ ዮሐንስ 4ኛ ከወደቁ በኋላ አፄ ምኒልክ ስልጣኑን ሲይዙ ከጣሊያን መልዕክተኛ ጋር የውጫሌ ውል ይፈራረማሉ፡፡ እንደሚታወቀው 17ኛው አንቀፅ ልዩነት ይፈጥራል፡፡
ብዙ ሰዎች ለአድዋ ጦርነት መንስኤ አድርገው የሚያቀርቡት ይሄን የውጫሌ ውል ነው፤ ግን የውጫሌ ውል ምክንያት አይደለም፡፡ የውሉ 17ኛው አንቀፅ ክብሪት ይጫር እንጂ ዋናው ምክንያት የኢጣሊያ የመስፋፋት ፍላጎት ነው፡፡ ጦርነቱ በዚህ መነሻ ከተካሄደ በኋላ አፄ ምኒልክ መረብን ተሻግረው ለመግፋት አልሞከሩም ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ጣልያን የያዘችውን ከመረብ ወዲያ ግዛት ኤርትራ ብላ ሰይማ ማስተዳደር ያዘች፡፡ የቅኝ ግዛት ያኔ ነው የሚጀመረው፡፡ ለ50 ዓመት በዚህ ሁኔታ ኤርትራ ቅኝ ግዛት ሆነች፡፡ ቀጥሎ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጣ፡፡ በዚህ ግዜ ጣሊያን ከጀርመን ጋር ወገነች፡፡ ከነሱ በተቃራኒ የተሰለፈችው እንግሊዝ፤ ኢትዮጵያ ነፃ እንድትወጣ ታደርግና ጃንሆይ ከስደት ተመልሰው መንግስታቸውን እንደገና ይመሰርታሉ፡፡ በዚህን ጊዜ ኤርትራ ከጣሊያን አገዛዝ ወደ እንግሊዝ ወታደራዊ አገዛዝ ትዞራለች፡፡ ለ10 ዓመታት ኤርትራ በእንግሊዝ ስር ነበረች፡፡ በዚህ አጋጣሚ የኤርትራውያን የነፃነት ታጋይ ድርጅቶች ብቅ ይላሉ፡፡ በሶስት ጎራም ይከፋፋሉ፡፡ አንደኛው “ከኢትዮጵያ ጋር መዋሃድ አለብን፤ ጠላቶቻችን ናቸው ቀድሞ የለዩን እንጂ እናት ሀገራችን ኢትዮጵያ ናት” የሚሉ የአንድነት ሃሳብ አራማጆች ናቸው፡፡ ሁለተኞቹ ነፃነትን፣ መገንጠልን የሚፈልጉ ሲሆኑ በአብዛኛው በዚህ ስብስብ ውስጥ የነበሩት ሙስሊሞች ናቸው፡፡ ይሄ ንቅናቄ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዘንድ ይደርሳል፡፡ አቶ አክሊሉ ሃ/ወልድ ያኔ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነበሩ፡፡ እሳቸው ግሩም የሆነ የፖለቲካ ጨዋታ ይጫወታሉ፡፡ ሶስተኞቹ መዋሃድ አለብን ግን ውል ልናስር ይገባል የሚሉ ናቸው፡፡ በመጨረሻ ሰፊ ክርክር ከተደረገ በኋላ በውል የሚለው ሃሳብ አሸነፈ፡፡ ኤርትራ መስከረም 1946 ዓ.ም በፌደሬሽን ትዋኃዳለች አንዱ የተመድ ተልዕኮ የኤርትራ ህዝብ ፍላጎት ባገኘው መሰረት ኤርትራ ነፃ ወጥታ የራሷን ውስጥ አስተዳደር መስርታ ከኢትዮጵያ ጋር በፌደሬሽን እንድትዋሃድ ይደረጋል፡፡
ከመጀመሪያውኑ የወቅቱ መሪ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ይሄን አለመፈለጋቸው እንግዲህ አንዱ የችግሩ መነሻ ነው፡፡ ለምን አልፈለጉም? ከተባለ፣ በኤርትራ ገና በመቋቋም በማደግ ላይ ያለ ቢሆንም ዲሞክራሲያዊ ስርአት ነበር፡፡ መድብለ ፓርቲ ያቆጠቆጠበት፣ የመናገርና የመፃፍ መብት ያለበት፣ ጠንካራ የሰራተኞች ማህበር የነበረበት ስርዓት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ያለው ደግሞ ፍፁማዊ ዘውዳዊ አስተዳደር ነው፡፡ ያ በህዝብ የተመረጠ ነው፡፡ እዚህ ያለው በመለኮታዊ ቅብአት የሚያምን ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሁለት መልክ ያላቸው ስርአቶች አብረው እንደማይሄዱ ዘውዳዊ ስርአቱን እንደሚያናጋው ጃንሆይ ተገንዝበውታል፡፡ ከመጀመሪያውኑ ፌዴሬሽኑን ለማፈራረስም ተንቀሳቀሱ በዚህ የተነሳ ፌደሬሽኑን ጠሉት፡፡
ይሄን የጃንሆይን ፍላጎት በተግባር ለመለወጥ ያገዟቸው ሁለት ኤርትራውያን ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት እንደራሴ የነበሩት ቢትወደድ አስፋው ወ/ሚካኤልና ቄስ ደሜጥሮስ ገ/ማርያም ናቸው፡፡ ይህን አቶ ዘውዴ ረታ በኤርትራ ጉዳይ መፅሃፋቸው ድንቅ አድርገው አስፍረውታል፡፡ የቢትወደድ አስፋው ዋና መከራከሪያቸው፤ “ፌደሬሽን ከኛ ልምድና የፖለቲካ ስርአት ጋር የሚጣጣም አይደለም፤ ቅኝ ገዥዎች የጫኑብን ነው፤ ስለዚህ መወገድ አለበት” የሚል ሲሆን ሌላው መከራከሪያቸው ደግሞ ፌደሬሽኑ በተራዘመ ቁጥር የኤርትራውያን የኢትዮጵያዊነት ስሜት እየተዳከመ ይሄዳል የሚል ነበር፡፡ ስለዚህ ይሄን ፌደሬሽን ማስወገድ አለብን የሚለውን አቋም አንፀባረቁ፡፡ እኚህ ሰው ዋና ተቃውሞአቸው የኤርትራ ዲሞክራሲያዊነትን ነበር የሚል እምነት አለኝ፡፡ እኚህ ሰው፤ “ይሄን ስናደርግ ጃንሆይ ይሄን አድርጉ ሳይሉን በራሳችን ተነሳሽነት ያደረግነው ቢሆንም የጃንሆይ ድጋፍ አልነበረንም ማለት አይደለም” ይላሉ፡፡ አቶ ዘውዴ ረታ ይሄን መነሻ አድርገው፣ ፌደሬሽኑን በማፍረስ ጃንሆይ ሊወቀሱ አይገባም፤ ተጠያቂው የኤርትራ ህዝብ ነው ብለዋል፡፡
በወቅቱ ቢትወደድ በኤርትራ ፓርላማ ቀርበው፤ “ይሄ ውስጣዊ አስተዳደር የሚባል ነገር የለም፤ አንድ መሪ አንድ መንግስት ነው ያለን” ብለው ፌደሬሽኑን አፈረሱት፡፡ ጉዳዩ ይፋ ሲደረግ ግን የኤርትራ ፓርላማ በስምምነት እንዳፈረሰው ተደርጎ ነው የቀረበው፡፡ የኤርትራ ችግር የሚጀምረው የፌደሬሽኑ መፍረስን ተከትሎ ነው፡፡ የመጀመሪያውና ትልቁ የኢትዮጵያ መንግስት ስህተት ይሄ ነው፡፡ ተመድን ሳያማክሩ በግላቸው ማፍረሳቸው ጥፋት ነው፡፡ ጃንሆይ በወቅቱ “ይሄ ነገር አይሆንም ተው” ያሏቸውን አማካሪዎቻቸውን የፀሐፊ ትዕዛዝ ወ/ጊዮርጊስ ወ/ዮሐንስና የአቶ አክሊሉ ሃ/ወልድን ምክር ቢሰሙ ኖሮ ለራሳቸውና ለመንግስታቸው፣ ለሀገራቸውና ለህዝባቸው ይበጅ ነበር፡፡ እኔ በማላውቀው ከፍተኛ ፖለቲካ ፌደሬሽኑ ይፍረስ ከተባለ ወሳኙ የኤርትራ ህዝብ ነው ይሄም ታዛቢዎች ባሉበት በሪፈረንደም ሲረጋገጥ ነው ይህ አልሆነም የኤርትራ ፓርላማም ፌደሬሽኑን ለማፍረስ የህዝቡ ይሁንታ አልነበረውም ፌደሬሽኑን በማፍረስ ተጠያቂው ንጉሰ ነገስቱ ናቸው፡፡ በዚህ መነሻ ነው እንግዲህ በኤርትራ የመገንጠል ሃሳብ ያነገቡ ድርጅቶች የተቋቋሙት፡፡
የማታ ማታ … ደርግን ለሽንፈት፣ አማፅያኑን ለድል ያበቃቸው ሚስጥር ምንድን ነው?
የሰላሙ በር ሲዘጋባቸው ኤርትራውያኑ ወደ ትጥቅ ይገባሉ፡፡ ኤርትራውያኑ በራሳቸው ሜዳ መዋጋታቸው፣ መልክአምድሩ (ኮንቬንሽናል) ለሁለገብ ጦርነት አመቺ አለመሆኑ፣ አማፅያኑ የውጭ ድጋፍ በተለይ ከኢራቅና ከሶርያ ያገኙ የነበረ መሆኑ እንዲሁም የሽምቅ ተዋጊዎቹ እምነት፣ ዲሲፕሊንና፣ የታጋይነት መንፈስና የአመራሩ ብስለት… ተጣምረው አሸናፊ አድርጓቸዋል፡፡
በኦጋዴን ጦርነት ጊዜ አማፅያኑ ሀገሪቱን ነፃ ለማውጣት የቀሯቸው 4 ከተሞች ብቻ ነበሩ፡፡ አስመራ፣ አሰብ፣ ምፅዋና ባሬንቱ ብቻ ነበሩ የቀሩት፤ ሌሎቹን ይዘዋቸው ነበር፡፡ በ1974 ዓ.ም የኢትዮጵያ መንግስት ሁለገብ ዘመቻ ያካሂዳል፡፡ በሶስት አቅጣጫ ሶስት ከባድ እዞች አሰልፎ አማፅያኑን ናቅፋ ላይ ለመጨፍለቅ ነበር አላማው፡፡ ሻዕቢያ መጨረሻ ላይ ከፍተኛ ፍልሚያ ያደረገው ናቅፋ ላይ ነበር፡፡ ከናደው እዝ ጋር ነበር የተፋለሙት፡፡ በወቅቱ ደርግ ናቅፋን 2 ኪ.ሜ ነበር ለመያዝ የቀረው ይባላል፡፡ ሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ “Red Tears” በሚለው መፅሃፉ ይሄ ተልዕኮ ስለከሸፈበት ሁኔታ ሲያብራራ፤ ዋናው ኢታማዞር ሹም ጀነራል ኃይለ ጊዮርጊስ ኃ/ማርያም (ዋናው ኢታማዦር ሹም) (መንግስቱ ቀደም ብሎ የ3ኛው ክ/ጦር ስለነበር) መንግስቱ ኃይለማርያምን ለማስደሰት ብሎ 17ኛ ክ/ጦር በያዘው ቦታ ቀድሞ 3ኛ ክ/ጦር እንዲገባ ትዕዛዝ ያስተላልፋሉ፤ ያቺን የጊዜ ክፍተት ተጠቅሞ ሻዕቢያ ይመታቸዋል፡፡ ይሄ ነው ሻዕቢያን ያተረፈው፡፡ ስለዚህ ሚስጥር በሚገባ ሊነግረን የሚችል የናደው ጦር አዛዥ የነበረው ውበቱ ፀጋዬ ብቻ ነው፡፡
ደርግ እንደ የቀይ ኮከብ ዘመቻ ከፍተኛ ኃይል አሰልፎ አያውቅም፡፡ የአየር ኃይል፣ የምድርና የባህር ኃይሉን ነበር በጋራ ያሰለፈው፡፡ የዕዝ ማዕከሉ ሁሉ ከአዲስ አበባ ወደ አስመራ ዞሮ ነበር፡፡ በሻዕቢያ በኩል ፍርሃት ይፈጠርና ከመደናገጥ ተነሳ ይመስላል ለታንዛኒያው ፕሬዚዳንት ጁሊየስ ኔሬሬ የያነጋግሩን መልዕክት ይልካል፡፡ ጁሊየስ ኔሬሬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸውን ወደ ኢትዮጵያ ይልኩትና ኢሳያስ እርቅና ንግግር እንደሚፈልግ ለመንግስቱ ይነግሩታል፡፡ ያኔ የታንዛኒያ የውጭ ጉዳይ የነበሩ ሣሊም ሣሊም ነበሩ መልዕክተኛው፡፡ እኔም ይሄን ጉዳይ ለማጣራት አንዴ አዲስ አበባ በመጡበት ወቅት ለ2 ሰዓት ያህል አነጋግሬያቸው ነበር፡፡ በወቅቱ የእርቅ መልዕክቱን ለመንግስቱ እንዳደረሱና መንግስቱ እንዳልተቀበላቸው ነገሩኝ፡፡ “ጦሩ በተጠንቀቅ ተሰልፏል፤ አሁን ተው ብንለው ሞራሉ ይሰበራል፤ ስለዚህ በጦርነት ነው የምንፈፅመው አለ መንግስቱ፡፡ ከጦርነቱ ፍፃሜ በኋላ ከአማፅያኑ ጥቂቶቹን በጦር በሰራዊታችን ውስጥ ልናስገባ እንችላለን አለኝ” አሉኝ፡፡ እንደኔ በወቅቱ በድጋሚ አንድ ወርቃማ እድል አምልጦናል፡፡ እንግዲህ በወቅቱ ጦርነቱ ተካሂዶ ውጤት አልባ ሆኗል፡፡ ሻዕቢያን የመጨፍለቅ አላማ ተሰናክሏል፡፡ ይሄ ለሻዕቢያ እንደ ድል የሚቆጠር ነው፡፡ የቀይ ኮከብ ዘመቻ ቢሰምር ኖሮ ለኢትዮጵያ የተለየ የታሪክ አጋጣሚ ይኖር ነበር፡፡ የነፃነት እንቅስቃሴው ላይቆም ቢችልም ቢያንስ በብዙ ዓመታት ወደ ኋላ ይጎትታቸው ነበር፡፡
ኢሣያስ በወቅቱ ለደርግ የእርቅ ጥያቄ ያቀረቡት ለጊዜ መግዣ ብለው ሊሆን አይችልም?
ጥሩ ግምት ነው፡፡ ሊሆን ይችላል፡፡ አይሆንም ማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን መንግስቱ ውጊያውን እንደሚያሸንፉ እርግጠኛ ስለነበር ያንን ጥያቄ አለመቀበሉ የሚያስገርም አይደለም፡፡
እንዲያ ከሆነ … ደርግን እንዴት መውቀስ ይቻላል?
በእርግጥ ጦሩ ከማይመለስበት ደረጃ ደርሷል ተብሏል፡፡ በቀይ ኮከብ ዘመቻ ብቻ በመሃል ያለቀው ወታደር ከ10 ሺህ በላይ ነው፡፡ 4 ወር ሙሉ ፅኑ ውጊያ አድርገዋል፡፡ ምንድን ነው ያከሸፈው የሚለውን ሊመልስልን የሚችለው፣ የጦሩ መሪ የነበረው ውበቱ ፀጋዬ ብቻ ነው፡፡ ይሄን ሃቅ ይዞ ከተቀበረ የኢትዮጵያ ታሪክ ተወቃሽ ሊሆን ይችላል፡፡ የቀይ ኮከብ ዘመቻ ቢሰምር ኖሮ ይሄን ቃለ ምልልስም ማድረግ ባላስፈለገን ነበር፡፡
የሻዕቢያና የህውሓት የትግል አጋርነት ምን ይመስል ነበር?
እንደሚታወቀው ህወሓት ከኤርትራው ትግል ተለይቶ አያውቅም፡፡ የኤርትራን ትግል እንደ ደጀኑ ነው ሁልጊዜ የሚያየው፡፡ ህውሓት፤ “ኤርትራ የኢትዮጵያ የቅኝ ግዛት ነች” ብሎ ሲነሳ ነው የኢትዮጵያን ሉአላዊነት የተፃረረው፡፡ በወቅቱ የህውሓት ህልውና የተቆራኘው ከኤርትራው እንቅስቃሴ ጋር ስለነበር ነው “ቅኝ ግዛት ነች” ያሉት፡፡ በአንፃሩም ያለ ህውሓት ድጋፍ ሻዕቢያ ሙሉ ለሙሉ ድል አይጎናፀፍም ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ተጋግዘው ነው “ኤርትራ ነፃ ወጥታለች” ያሉት፡፡
ኤርትራ ነፃነቷን ካገኘች በኋላም በሁለቱ ሀገራት መካከል እስከ ዛሬ ድረስ ግጭቶች ያልቆሙት ለምንድን ነው?
ሻዕቢያና ወያኔ ተባብረው ነው የኢትዮጵያን ጦር ኃይል የደመሰሱት፡፡ ከዚያ በኋላ ጦሩ እንደ ትቢያ ነው የተበተነው፡፡ ከድላቸው በኋላ በ1983 አዲስ አበባ ላይ የሽግግር መንግስት ሲቋቋም ኢሣያስ በታዛቢነት ነበር የተቀመጠው፡፡ ሻዕቢያና ወያኔ በትግሉ ጊዜ ብዙ ልዩነት ነበራቸው፡፡ ከጦርነት አፋፍም የተመለሱበት ጊዜ ነበር፡፡ ከድሉ በኋላ በተለያዩ መስኮች ስምምነት መፈራረም ጀምረው ነበር፡፡ እስከ 7 ዓመት የሚዘልቅ የኢኮኖሚ፣ ወታደራዊ ፖለቲካዊ ስምምነቶችን ተፈራርመዋል፡፡
የድንበሩ ጉዳይ ምን ይሁን ሲባል የጋራ ኮሚሽን አቋቁሙ፡፡ ኮሚሽኑ ስራውን እየሰራ ሳለ የኤርትራ መንግስት በታንክና በመድፍ የታጀበ ሰራዊት ልኮ ባድመንና ሽራሮን በከፊል ያዘ፡፡ የጦርነቱ መንስኤ ይህቺ ብትሆንም ለ1991 የሁለቱ ሀገራት ጦርነት ባድመ እንደ ምክንያት ሆነች እንጂ ምክንያቶቹ ሌሎቹ ናቸው፡፡ ከነፃነታቸው በኋላ … ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖራቸው የንግድ፣ የመግባብያ ገንዘብ፣ የኤርትራውያን ዜግነት ጉዳይ የመሳሰሉትን መፍትሄ አላበጁለትም ነበር፡፡
የናቅፋ ገንዘብ ጉዳይ፣ የወደብ ጉዳይ ብዙ ችግር ነበረበት፡፡ ለዚህ ቀውስ እንደ እሳት ማቀጣጠያ ክብሪት የተጠቀሙት ባድመን ነበር፡፡ እንግዲህ በዚህ ጦርነት ከ70-100 ሺህ የሚገመት የሰው ህይወት ጠፍቷል ይባላል፡፡ በጦርነቱ አሸነፈና ባድመን ተቆጣጠረ፡፡ ጉዳዩም ወደ አልጀርስ ሄዶ የአልጀርስ ስምምነትን ይፈራረማሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በራስ መተማመኑ አይሎ ይመስለኛል … “የአልጀርሱን ስምምነት ያለ ይግባኝ እንቀበላለን” ብሎ ፈረመ፡፡ ይሄ ትልቁ ስህተት ነበር፡፡ ባድመ ለኤርትራ ተፈርዳ ሳለ፣ የኛ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉዳዩን በግልፅ ሳያጣሩ፤ “በጡንቻችን ያስመለስናትን ባድመን በህግ አረጋግጠነዋል” አሉ፡፡ በኋላ ባድመ ለኤርትራ መሰጠቷን የኢትዮጵያ መንግስት ሲረዳ ባድመን አልለቅም አለ፡፡ ድንበሩን ከማስመራችን በፊት ባሉት ችግሮች ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መነጋገር አለብን የሚል አቋም የኢትዮጵያ መንግስት ያዘ፡፡ የኤርትራ መንግስት በበኩሉ፤ “የለም መጀመሪያ ከባድመ ውጡና በጠረጴዛ ዙሪያ እንገናኛለን” ይላል፡፡
ይሄ ነው እንግዲህ ላለፉት 18 ዓመታት መቋጫ ያላገኘው ንትርክ መንስኤ፡፡ አሁን ያለው ቀዝቃዛ ጦርነት የዚህ ውጤት ነው፡፡ ሀገራቱ ይሄ ግትርነት እስካለ ድረስ ተፋጠው ነው የሚቀጥሉት፡፡ በቅርቡ የተፈጠረው ትንኮሳም የዚሁ ውጤት ነው፡፡
ከሰሞኑ የኤርትራ መንግስት ትንኮሳ ተፈፀመብኝ ብሎ ለተባበሩት መንግስታት በቅድሚያ አቤቱታ አቅርቧል … በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
መልሴ እንግዲህ ግምታዊ ነው የሚሆነው፡፡
ምንም የተጨበጠ ነገር የለም፡፡ ሁለቱም መንግስታት በዝርዝር የሚገልፁት ነገር የለም፡፡ በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በኩል የኤርትራን መንግስት በተመለከተ ሪፖርት መውጣቱ፣ እንደገና “የኢትዮጵያ መንግስት ሊወረኝ ነው” የሚለው ጩኸት ከየት መጣ ብለን መጠየቅ አስፈላጊ ነው፡፡ የሆነ የተቀናበረ ነገር ያለ ይመስላል፡፡
እናንተም ያነጋገራችኋቸው ጀነራል አበበ ተ/ሃይማኖት፤ ኤርትራ ገብተን ኢሣያስን ማስወገድ አለብን ነው ያሉት፡፡ እኔ ይሄ አማራጭ ሊሆን አይገባም ባይ ነኝ፡፡ አልሻባብን እንደወጋነው ኢሳያስንም ማስወገድ እንችላለን ማለት … አሸባሪ ቡድንና ብሄራዊ መንግስትን ነጥሎ ያለማየት ይመስለኛል፡፡
የኤርትራ ብሄራዊ መንግስት ነው፤ በሶማሊያ ያለው አሸባሪ ቡድን ነው፡፡ የአንድን ሀገር ብሄራዊ መንግስት እንዴት እናስወግድ ይባላል፡፡
እንኳን ብሄራዊ መንግስትን ለማስወገድ ይቅርና ከ10 ዓመት በፊት እናስወግደዋለን ያልነውን ተራ አሸባሪ ቡድን እንኳ ሙሉ ለሙሉ መደምሰስ አልተቻለም፡፡ አልሻባብ ዛሬም በሶማሊያ ህይወት አለው፡፡ የኤርትራን መንግስት እናስወግድ ስንል ምን አዘጋጅተን ነው? የኤርትራ ተቃዋሚዎች አሉ ከተባሉ ደካማዎች ናቸው፤ ወጣቶቿ በስደት መከራ የሚበሉ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል የሻዕቢያ መንግስት ምን ያህል ነው የሚያሰጋን? ጠንካራ አይደለም፤ ስለዚህ በኢትዮጵያ ላይ ጥይት ለመተኮስ አይደፍርም ባይ ነኝ፡፡ ከተኮሰም መቃብሩን ቆፈረ ማለት ነው፡፡ ከአሁን በኋላ በአካባቢው ጥይት ተተኮሰ ከተባለ መጀመሪያ ሊተኩስ የሚችለው የኢትዮጵያ መንግስት ነው፡፡
የኤርትራ መንግስት ጠንካራ አይደለም ከተባለ ለምንድን ነው ታዲያ በቀላሉ ማስወገድ የማይቻለው?
የኤርትራ ህዝብ መንግስቱን ቢጠላ ሀገሩን አይጠላም፡፡ ሀገሩን ይወዳል፡፡ ሀገሩ በሌላ ጦር ስትወረር ዝም ብሎ አያይም፡፡ ሁለተኛው እናስወግድ ቢባል እንኳ በሀገሪቱ ስልጣን ተረክቦ ሊመራ የሚችል ጠንካራ ተቃዋሚ ባለመኖሩ ሀገሪቱ የአሸባሪዎች መናኸሪ ልትሆን ትችላለች፡፡ ያን ጊዜ ደግሞ ኢትዮጵያ በሁለት በኩል ትወጠራለች ማለት ነው፡፡ ስለዚህ መንግስቱን የማስወገድ ኃላፊነት የኤርትራ ህዝብ ብቻ ነው፡፡ ድጋፍ ግን አያስፈልጋቸውም ማለት አይደለም፡፡ በኃይል ሳይሆን በሌላ ነገር መደገፍ ይቻላል፡፡ ከታሪክ እንደምናውቀው መንግስታት የሚጠቀሙት ስልት ነው፡፡
ከኤርትራ ጋር በተያያዘ በአሁን ወቅት ለኢትዮጵያ አሳሳቢ የሚሆነው ምንድን ነው?
ኤርትራ እንደሚታወቀው ህገ መንግስት የሌላት ሀገር ነች፤ የመናገርና የመፃፍ፣ የመሰብሰብ መብት የሌለባት በአንድ ሰው ፍፁማዊ አገዛዝ ስር ያለች ሀገር ነች፡፡ ኢኮኖሚዋ የደቀቀ ነው፡፡ መንግስቷ ከዓለም ማህበረሰብ የተገለለ፣ በአንድ እግሩ የቆመ መንግስት ነው፡፡ ይህ አይነቱ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ይከፍታል የሚል ግምት የለኝም፡፡ ለራሱ ደህንነት ሲል የሚያደርግ አይመስለኝም፡፡ በአንፃሩ የኢትዮጵያ መንግስት ከኤርትራ አንፃር ሲታይ ጠንካራ መንግስት ነው፡፡ በኢኮኖሚው፣ በወታደራዊ ኃይሉ የተሻለ ነው፡፡ ከአፍሪካ ቀንድ ጡንቸኛው ሰራዊት ነው፡፡ ስለዚህ በኔ ግምት የመጀመሪያዋን ጥይት ሊተኩስ የሚችለው የኤርትራ ሳይሆን የኢትዮጵያ መንግስት ነው፡፡ የውስጥ ችግሩንም ለማርገብ የኢትዮጵያ መንግስት ይሄን አማራጭ ሊጠቀም ይችላል፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል “ሰላምም ጦርነትም” አለመኖሩ ለመንግስታቱ የሚጠቅመው ነገር ይኖር ይሆን?
በኤርትራ በኩል መንግስታቸው “ህዝቡን ልትወረር ነው፣ ሀገር ልትደፈር ነው፣ ሉአላዊነትህ ሊጣስ ነው” በማለት እያስፈራራ የፖለቲካ ህይወቱን ያስቀጥልባታል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትም ውስጣዊ ውጥረቶች አሉበት፡፡ እነዚህን ለማርገብ እየፎከረ የህዝቡን ቀልብ ይስብባታል፡፡
ከዚህ ችግር መውጭያ መፍትሄው ምንድን ነው?
መፍትሄው ጦርነት ሳይሆን ንግግርና ውይይት ነው፡፡ ይሄን ለማድረግ ደግሞ በሁለቱም ሀገራት የዲሞክራሲ መስፋፋትን ይጠይቃል፡፡ የሚደረገው ስምምነት እንደ አልጀርሱ ሳይሆን ዜጎችን ማሳተፍ አለበት፡፡ አገራቱን ከጦርነት የሚታደጋቸው ሌላ አካል አይኖርም፡፡ በተለይ የምዕራባውያን መንግስታት፣ ኤርትራና ኢትዮጵያን የቼዝ መጫወቻ እንዳያደርጓቸው መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡
የመጨረሻው መፍትሄ የሰላም ድርድር ብቻ ነው፡፡
የሁለቱ ሀገራት ህዝብ፣ በሃይማኖት፣ በባህል፣ በኢኮኖሚ የተሳሰረ ነው፡፡ የቻይና ግንብ በመገንባት መለየት አይችልም፡፡
ልቦና ያላቸው መንግስታት ከመጡ የፈረሰው ፌደሬሽን ተመልሶ ይገነባ ይሆናል፤ ካልሆነም በኮንፌዴሬሽን እንደምንተሳሰር እኔ ተስፈኛ ነኝ፡፡ ይሄ እንደኔ ሩብ ክፍለ ዘመን የሚፈጅ አይመስለኝም፡፡ ኢሣያስ 25ኛ ዓመት የነፃነት በአላቸው ላይ ባደረገው ንግግር፤ ለወርቃማው በዓል ያገናኘን ብሏል፡፡ ለኔ ይሄ ከቅዠት ያለፈ አይደለም፡፡ 25 ዓመት ባልሞላ አጭር ጊዜ ውስጥ ሁለቱ ሀገራት በኮንፌደሬሽን ሊተሳሰሩ ይችላሉ፡፡ ዋናው አዕምሮና ብልህነት ያለው መንግስት መምጣቱ ነው፡፡
በኛ ሀገር ያለው የተቃውሞ ፖለቲካ ብዙ ጊዜ ኤርትራ መገንጠል አልነበረባትም ከሚል ቁጭት መነሳቱ ለኤርትራውያን የሁልጊዜ ስጋት አይሆንባቸውም? በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
አንዳንዱ ኤርትራዊ የኢሳያስን ቃል እንደ መፅሀፍ ቅዱስ ቃል ያምናል፡፡ ብዙው ደግሞ ይሄ ነገር እየተደጋገመ ሲነገር ሲሰማ ስጋት ያድርበታል፡፡ ያገኘነውን ነፃነት ልናጣ ነው ብሎ ይሰጋል፡፡ የኤርትራ ብሄርተኝነት ከፍ ያለ ነው፡፡ ኤርትራ ነፃ የወጣችው በኢትዮጵያ መንግስታት ስህተት ነው፡፡ መጀመሪያ ፌደሬሽኑን በማፍረሳቸው ጦርነት ውስጥ ተገባ፡፡
ደርግ ደግሞ የቀረበለትን መልካም እድል ገፍቶ ሄዶ ተሸነፈ፡፡ ስለዚህ ኤርትራውያኑ ነፃነታቸውን ያገኙት በጡንቻቸው ነው፡፡ ታዲያ በጡንቻቸው ያገኙትን ነፃነት ስናናንቅባቸው ስጋት ሊገባቸው ይችላል፡፡ ይሄ ደግሞ አሁን ያለውን መንግስታቸውን ሊያጠናክረው ይችል ይሆናል፡፡ የኤርትራ መንግስት የትግሉ ዘመን ወኔ እየደቀቀ ቢሆንም፣ የኤርትራዊነት ስሜት ግን ከህዝቡ ተሸርሽሯል ማለት አይደለም፡፡
ኢትዮጵያ ያለ ወደብ መኖር አትችልም፤ የአሰብ ወደብም ይገባታል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ይሄን ወደብ መልሰን የራሳችን የምናደርግበት እድል ይኖራል ብለው ያስባሉ?
እኔ በወደቡ ጉዳይ አሰብ የኛ ነች ከሚሉት የተለየ አቋም ነው ያለኝ፡፡ እሱ የኛ ነች ይላል፡፡ የመጠቀም መብት አለን ከሆነ ያስኬዳል፤ ትክክል ነው የመጠቀም መብት አለን፡፡ ከወደቦቹ ባለቤት ጋር የኢትዮጵያ መንግስት መስማማት አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ተዘግታ መኖር የለባትም፡፡ በአሰብም በምፅዋም የመጠቀም መብት አለን፡፡ ኢትዮጰያ ካልተጠቀመችባቸው ደግሞ እነዚህ ወደቦች ለኤርትራ ጥቅማቸው እምብዛም ይሆናል፡፡ ለዚህ ነው ኮንፌደሬሽን መምጣቱ አይቀርም የምለው፡፡
አሰብን በመጀመሪያ ለጣሊያን የሸጠው የዚያው አካባቢ ሰው ነው፡፡
ከዚያ ጣልያን ከኤርትራ ጋር ጠቅልሎ ያዛት፡፡ ለብቻዋ የቀረች አልነበረችም፡፡ ታዲያ እንዴት ነው አሰብን ብቻ ነጥለን አውጥተን የኛ ነች ማለት የሚቻለው፡፡ ይሄ በአለማቀፍ መርሆች አያስኬድም፡፡ የመጠቀም መብት እንዳለን ሜ/ጀነራል አበበ ተ/ሃይማኖት በሰላም መጠቀም እንችላለን ባለው ሃሳብ እስማማለሁ፡፡
የመጠቀም መብት አለን ሲባል እንዴት ነው? እንደ ጅቡቲ ወደብ ማለት ነው?
ለዚህ ሁለቱ መንግሥታት የሚያደርጉት ስምምነት ነው የሚወስነው፡፡ ውላቸው ወሳኝነት አለው፡፡ በኪራይ ነው? በጥቅማጥቅም ነው…? የሚሉትን የሁለቱ አገራት ድርድር ይወስነዋል፡፡
ኢትዮጵያ የመጠቀም መብቷን፣ ኤርትራም የወደቦቹን የባለቤትነት መብት ተጠቅመው የሚሰሩበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ የመብትና ግዴታ ጉዳይ ሁለቱ ሀገራት በውይይት ሊጨርሱት ይገባል፡፡
ሁለቱ አገራት አሁን ያላቸውን የጦር አሰላለፍ እንዴት ይገመግሙታል?
አሁን ያጠናሁት ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ከማነበው ተነስቼ ብናገር፣ የኢትዮጵያ ጡንቻ ይበልጥ ፈርጥሟል፡፡ የኤርትራ በአንፃሩ የተዳከመ ይመስላል፡፡
ወጣቶቹ እየተሰደዱ ነው፡፡ እንግዲህ የሳዋው ስልጠና ፋይዳ ቢስ እየሆነ ነው ማለት ነው፡፡
“ለኤርትራ መገንጠል ተወቃሾቹ የኢትዮጵያ መንግስታት ናቸው” ብለዋል፡፡ አሁን ላይ ይሄ ቢሆን ኖሮ ማለቱ ምንድነው ጥቅሙ? የፌደሬሽኑ መፍረስ የመሳሰሉት ጉዳዮችን ማንሳቱ ምንድነው ፋይዳው?
ይሄ ታሪክ የምንማረው ለምንድነው እንደ ማለት ነው፡፡ ከየት ተነስተን እዚህ ደረስን? እዚህስ ያደረሱን እነማን ናቸው? በዚያ ሂደት አቀበት ቁልቁለት ነበረበት፡፡ የታሪክ ዘገባ የሚፃፈው ሀገር ተረካቢው እሱነቱን እንዲያውቅና ስለሚረከባት ሀገር ማወቅ ስላለበት ነው፡፡ ደርግና ኢህአፓ ለምንድን ነው እንደዚያ የሆኑት? ጃንሆይስ የሰሩት ስህተት ምንድን ነው? የመሳሰሉትን መጪው ትውልድ ማወቅ አለበት፡፡
የአሜሪካ የእርስ በእርስ ጦርነት በሰሜኑና በደቡብ፤ በፌደራሊስትና በኮንፌደራሊስት፣ በአንድነት ባዮችና በተገንጣዮች መካከል ነበር፡፡
4 ዓመት ሙሉ ተዋግተዋል፡፡ የጠፋው 1 ሚሊዮን ህዝብ ነው ይባላል፡፡ ሰሜኑ ድል ተጎናፀፈ፡፡
ከዚያ በኋላ ግን እዚህ እንደሚደረገው ይሄን ድል 21 መድፍ በመተኮስ አይደለም የሚዘክሩት፡፡
ወንድማማቾች ናቸው የተጋደሉት፡፡
በየሸንተረሩ በየአፈሩ የተቀባበሩት ወንድማማቾችና እህትማማቾች ናቸው፡፡ በየዓመቱ 21 መድፍ መተኮስ ለእርቅና ለሰላም የሚበጅ አይደለም፡፡
ይሄን መንግስት ማወቅ አለበት፡፡ አንዱ ሲደሰት የሌላውን ወታደር ቤተሰብ ቁስል እየቦረቦረ መሆኑን መረዳት አለብን፡፡ ስለዚህ እኔ ይሄ መድፍ ትኮሳው መቆም አለበት ባይ ነኝ፡፡
የአሜሪካ የእርስ በእርስ ጦርነት አብቅቶ አንድ ከሆኑ በኋላ የአሜሪካ የታሪክ ፀሐፍት የሚስማሙበት አንዱና ዋነኛው ጉዳይ፤ የእርስ በእርስ ጦርነቱ አሜሪካን ፈጥሯል የሚለውን ነው፡፡
ዛሬ ላይ ያለችውን ሃያሏን አሜሪካን የፈጠረው ያ ጦርነት ነው፡፡ የኛ የእርስ በእርስ ጦርነት ውጤቱ፡- ኤርትራን አስገነጠለ፤ ወደብ አልባ አደረገን፡፡ ቢሆንም የተመሰረተው የፌደራል ስርአት በኔ በኩል ለህዝቦቿ ለሀገሪቱ ጠቃሚ ነው፡፡
ይሄ እምነቴ ነው፡፡ የደርግ የመሬት አዋጅ የደርግ መልካም ቅርሱ ነው፡፡ የዚህ መንግስት ዋናው ቅርሱ ደግሞ አሁን ያለው የፌደራል መዋቅሩ ነው፡፡ ስለዚህ ታሪክ የምንማረው ያለፈውን አውቆ ያሁኑን ተረድቶ የወደፊቱን ለማለም ነው፡፡ የታሪክ ዋናው ፋይዳው ራስን ለማወቅ ስለሚረዳ ነው፡፡

Pages: 1