ሄሎ ሀበሻ ምርጥ የሀበሻ መዝናኛ ሰፈር፣
ይህ ዌብ ሳይት ሀበሻን ከመላው አለም በማገናኘት የሚያወያይ
የሚያዝናና ዌብ ሳይት ወይም መድረክ ነው፥፥
ተሳተፉ ፣ ኮመንት አድርጉ ፣ የራሳችሁን ፃፉ
0 users browsing Personal Blog የመጣጥፍ ቦታ. | 1 guest
Pages: 1
Posted on 06-11-19, 05:48 pm


Karma: 100
Posts: 765/769
Since: 03-20-17

Last post: 379 days
Last view: 379 days
የሞት ነጋዴው መታወሻ!
ከዓመታት በፊት የሆነ ነው...
አንድ ጎልማሳ በመኖሪያ ቤቱ ወንበሩ ላይ በምቾት ለጠጥ ብሎ ተቀምጦ የእለቱን ጋዜጣ እያነበበ ነበር። ጋዜጣው እንደተለመደው ትኩስና መረጃ አዘል ዜናዎችን ይዞ ወጥቷል። ጎልማሳው አይኑን በጋዜጣው ላይ እያንከባለ፣ ከአንዱ ርዕስ ወደ ሌላው እየዘለለ፣ ምን ምን ጉዳዮች እንደተከናወኑ እየተመለከተ ጥቂት ገፆችን እንዳገላበጠ፣ ሰበር የሞት ዜናዎች የሚቀርቡበት አምድ ላይ ሲደርስ፣ በድንገት የራሱን ሥም ሲመለከት ድንጋጤ አዘልሎት ኮርኒስ አስነካው። ጋዜጣው በስህተት ያወጣው ዜና የሚያስነብበው መረጃ ስለጎልማሳው መሞት ነበር። ጎልማሳው የራሱን ሞት ከጋዜጣው ላይ ሲያነብብ አይኑን ማመን አልቻለም። ለደቂቃዎች በድንጋጤ ውስጥ ከቆየ በኋላ ወደራሱ ሲመለስ፣ ሰዎች የእርሱን ሞት ተከትሎ ስለእርሱ ምን እንዳሉ ለማወቅ ጉጉት አደረበትና ማንበቡን ቀጠለ...
የአደጋ ዜናው እንዲህ የሚሉ ሐሳቦችን ይዟል...
“የድማሚቱ ንጉስ ሞተ….”
“ሰውዬው የሞት ነጋዴ ነበር” ይላል ጋዜጣው።
ይኽ ሰው፣ የፈጠራ ባለሙያውና ‹‹ድማሚትን›› ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም ያስተዋወቀው ‹‹አልፍሬድ ኖቤል›› ነው። ታዲያ ከጋዜጣው ላይ ‹‹የሞት ነጋዴው›› የሚለውን ሀረግ ሲመለከት ግራ በመጋባት “በቃ! እንደዚህ ነው ሰዎች የሚያስታውሱኝ?” ሲል ራሱን ጠየቀ። ይኼንን በፍፁም አልጠበቀም ነበር። ያገሩ ሰዎች ‹‹የሞት ነጋዴ›› አድርገው እንደሚያስቡት እንዴት ሊጠረጥር ይችላል? ግን ሆነ... የሰው ልጆችን ሊጠቅም ለዘመናት ተመራምሮ የሠራው ቴክኖሎጂ ሳያስከብረው ቀረ... በርግጥ በገንዘብ ደረጃ የናጠጠ ሀብታም አድርጎታል... ችግሩ ግን ለዓለም ያበረከተው ያ ፈጠራው በመጥፎ ታየ... ሰዎች ልፋቱን በክፋት ተረጎሙበት...
ይኼን ታሪኩን መቀየር አለበት። አዎ! የሞት ነጋዴ እየተባለ መሞት የለበትም። አልፍሬድ፣ ቀኑን ሙሉ ሲያውጠነጥን ውሎ አመሻሽ ላይ ወሰነ። ከዚያን እለት ጀምሮ ለዓለም ሰላም መሥራት ጀመረ... ገንዘቡን ሰብስቦ ሰጠ... ጥረቱም ፍሬ አፈራለነት… እነሆ ዛሬ ዓለም ሁሉ የሚያስታውሰው ከሽልማቶች ሁሉ ትልቅ በሆነው ‹‹የኖቤል ሽልማት›› ነው። ዓለም ላይ የሚገኙ ታላላቅ ሰዎች፡ በፊዚክስ፣ በኬሚስትሪ፣ በህክምና፣ በሥነ-ፅሁፍ እና በሰላም ዙሪያ ታላቅ ገድል የሠሩ ሰዎች ተመርጠው የሚሰጣቸው ታላቅ ሽልማት ነው። እነሆ ሽልማቱ ከተጀመረ መቶ ዓመታት አልፈውታል። “የሞት ነጋዴ” ተብሎ የነበረው አልፍሬድ ኖቤልም እንደ ፍላጎቱ እጅግ ከፍ ባለ መልኩ እየታወሰበት ይገኛል።
#ለመሆኑ_እኛስ
ከሞታችን በኋላ እንዴት እንታወሳለን?
መቸም ከአዳም ተፈጥረን ሞት አይቀርልንምና ሁላችንም የምድርን የሞት ፅዋ ቀምሰን ወደምንሄድበት መሄዳችን የማይቀየር የተፈጥሮ ህግ ነው። ምድር ላይ ግን ምን ጥለን ነው የምንሄደው? መጽሀፍ ጽፈናል? ስዕል ስለናል? ቅኔ ዘርፈናል? ዜማ ደርሰናል? ህንጻ አንጸናል? ድልድይ ገንብተናል? ሕዝብን በመልካም መንገድ መርተናል? አስተምረናል? በሳይንስ ተራቅቀናል? ቴክኖሎጂ ፈጥረናል? በሕይወት ዘመናችን ምን ሠርተናል?
ሶቅራጠስ በጠያቂ ማንነቱና በፍልስፍናው ይታወሳል። አልበርት አንስታይን በፊዚክስ ተጠብቦ፣ ከአቶም እስከ ጠፈር ተመራምሮ የተፈጥሮን ህግ በቀመር ስለገለጠ ሥሙ በመዛግብት ላይ ብቻ ሳይሆን በአለም ህዝቦች ልብ ውስጥ ታትሞ ተቀምጧል። ቶማስ ኤዲሰን ከኤሌክትሪክ ብርሃንን መፍጠር ስለቻለ ለዓለም ብዙ ውለታ የዋለላት ጀግና የፈጠራ ሰው ተደርጎ ይታሰባል። ኔልሰን ማንዴላ የደቡብ አፍሪካ ጥቁሮችን ከአፓርታይድ ሥርዓት ነጻ አውጥቶ፣ የዘር መድሎን አስቀርቶ፣ በህዝቡ መካከል እርቅን ስላወረደ ‹‹የይቅርታ አባት›› ተደርጎ በሰዎች ዘንድ ሲታወስ ይኖራል። ማህተመ ጋንዲ ህንድን ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ነጻ ሲያወጣ ምንም ጦር መሳሪያ ባለመጠቀሙ ‹‹የሰላም አባት›› እየተባለ ይኖራል።ቀዳማዊ ኃይለስላሴን በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ፣ ዐጼ ምኒሊክንና እቴጌ ጣይቱን በአድዋ ድል፣ ዐጼ ዮሀንስ አራተኛን በመተማው ጦርነት፣ ዐጼ ቴዎድሮስን በሴፓስቶፖል መድፍ... እናስታውሳቸዋለን። አለቃ ገብረሐና- ብልህነታቸው፣ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ- መለኛነቱ (አባ መላ)፣ አብዲሳ አጋ- ጅግንነቱ... ከሌላው ነገር ሁሉ ቀድሞ ወደ አእምሯችን የሚመጣው ይኼ ነው።
#መታወስ_የምንፈልገው_በምን?
እኛስ በምንድን ነው መታወስ የምንፈልገው? በደግነታችን ነው ወይስ በክፋታችን? በማዳናችን ነው ወይስ በመግደላችን? በፍርሃታችን ነው ወይስ በድፍረታችን? በቸርነታችን ነው ወይስ በንፉግነታችን? ትውልድን በመቅረፃችን ነው ወይስ ትውልዱን ባልሆነ መንገድ በመውሰዳችን? በምንድን ነው መታወስ የምንፈልገው? አንዳንዶች በሙያቸው ለሰው ልጆች ባበረከቱት አስተዋጽኦ መታሰብ ይፈልጋሉ። ለምሳሌ፡ ያገራችን የሙዚቃው ንጉሥ ጥላሁን ገሰሰ፣ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ከነገሠበት የኢትዮጵያ ሙዚቃ ብቻ ሳይሆን ለስድሳ ስምንት ዓመት በሥጋ ከተመላለሰበት ዓለም በሞት ከመሰናበቱ ቀደም ብሎ በምን መልኩ መታወስ እንደሚፈልግ ምኞቱን በዜማ እንዲህ ሲል ገልፆታል።
…ዜማ እንጉርጉሮዬ፣ የግሌን ቅላፄ
ተቀርፆ ይቀመጥ ታሪኬ ነው ድምፄ
ድምፃዊ ዘፋኝ ነኝ አንጎራጉራለሁ
ይኼ ነው ታሪኬ ሌላ ምን አውቃለሁ…”
ጥላሁን በዜማው እንደተናዘዘው መታወስ የሚፈልገው በሙዚቃው ነው። በድምፃዊነቱ የሀገሩን ውበት ሲያሞግስ እንደኖረ እና ከዚያ የተለየ ታሪክ እንደሌለውና እንዲኖረው እንደማይፈልግ አስረግጦ ይገልፃል። መልካሙም ነገር ጥላሁን ምኞቱ ተሳክቶለታል... እኛ ኢትዮጵያውያን ጥላሁንን አሁን የምናስታውሰው በአንጋፋ ድምፃዊነቱ እንጂ በሌላ አይደለም። ልጅ ሆነን በቃላችን “አውሮፕላን መጣ እየገሰገሰ፣ በዘፈን አንደኛ ጥላሁን ገሰሰ...” ስንላት የነበረችው ግጥም ዛሬም ስለጥላሁን ስናስብ ቀድማ ወደ ልባችን የምትመጣው እሷ ናት። ጥላሁን ሙዚቃን ሲጫወተው ጥሩ አድርጎ አንዴ ድምፁን ዝቅ፣ አንዴ ደግሞ ከፍ እያደረገ፤ አንዳንዴ በፈገግታ፣ አንዳንዴም በእንባ ታጅቦ ሲዘፍን፣ ለሙዚቃ ነብስ አልብሷት ስናየው፣ እውነትም አንደኛ እንላለን። ከሞተም በኋላ ጥላሁንን በዚያ ድምፁ፣ ግርማ ሞገስ በተላበሰው በዚያ ያዘፋፈን ስልቱ እናስታውሰዋለን። ጥላሁንም ምኞቱ ሰመረለት... እንደፍላጎቱ በሙያው አስታወስነው...
#መታወስ_እንደፍላጎት_ባይሆንስ?
መቸም ጥላሁን ሙዚቀኛ ብቻ አልነበረም...
ታዲያ በግል ህይወቱ ጥላሁን ምን አይነት ባህሪ ነበረው? ደግ ነበር ክፉ? ታማኝ ነበር አጭበርባሪ? አናውቅም። ከግል ህይወቱ የበለጠ የሙዚቃ ህይወቱ ስለገነነ እንደምኞቱ ሰዎች የሚያስታውሱት በሙዚቃው ሆነ እንጂ ከግል ህይወቱ አንድ አስቀያሚ ባህሪው ወይም ተግባሩ ተነግሮ (አይበለውና) በዚያ ሲታወስ እንደሚኖር ቢገነዘብ ጥላሁን ምን ሊሰማው ይችላል?
‹‹አልፍሬድ ኖቤል›› ድማሚትን ሲፈጥር ፍላጎቱ የነበረው፣ አልገራ ያለውን ተፈጥሮ ለመግራት... ተራራውን ደረማምሶ ሜዳ ለማድረግ እንዲያገለግል አስቦ ሊሆን እንደሚችል ጥርጥር የለውም። ዳሩ ግን ሌሎች ሰዎች ድማሚትን ሲጠቀሙት የሰው ህይወትን ለመቅጠፍ ሆነና የድማሚት ፈጣሪው አልፍሬድ “የሞት ነጋዴ” ተባለበት። በዚህ ምክንያት የእሱ ፍላጎት እና ሰዎች የሚያስታውሱበት መንገድ ተለያይቶ ተገኘ።
ክፍል ሁለት ይቀጥላል
Pages: 1