ሄሎ ሀበሻ ምርጥ የሀበሻ መዝናኛ ሰፈር፣
ይህ ዌብ ሳይት ሀበሻን ከመላው አለም በማገናኘት የሚያወያይ
የሚያዝናና ዌብ ሳይት ወይም መድረክ ነው፥፥
ተሳተፉ ፣ ኮመንት አድርጉ ፣ የራሳችሁን ፃፉ
0 users browsing Movies. | 1 guest
Pages: 1
Posted on 12-25-17, 08:37 am


Karma: 90
Posts: 663/879
Since: 02-29-16

Last post: 92 days
Last view: 92 days
ፊልሞቻችን የገሀዱ ዓለም ነፀብራቅ ወይስ የውጭ ባህል ማራገፊያ?

ገሀዱ ዓለም ሌላ፣ የሚሰራልን ፊልም ደግሞ እንዲሁ ሌላ እየሆነ መጥቷል። በተለይም ባህልን ያማከለ ተግባር ከማከናወን አንጻር ብዙዎቹ የአገራችን ፊልሞች ገንዘብ ተኮር መሆናቸው እሙን ነው። ታዲያ ይህንን ማን መፍትሄ ይስጠው? በምን መልኩስ መዳኘት አለበት። እውነት እንደተባለው ይህ ብቻ ነው ችግሩ ወይስ ሌሎች መሰናክል የሆኑት ጉዳዮች አሉና መሰል ጭብጦችን በማንሳት የፊልም ኢንዱስትሪው ማበርከት ያለበትን ያህል እንዲችል ለማድረግ የፌዴራል ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሰሞኑን በጉዳዩ ዙሪያ ባለሙያዎችን በመጋበዝና አጥኚዎች በመረጃ የተደገፈ ጽሑፍ ለባለድርሻ አካላት እንዲያመላክቱ አድርጓል።ይሁንና ስንቱ ተማረበት መልሱ ለታዳሚው ይሆናል? በእርግጥ አሁንም አንድ ነገር ሳልል ማለፍ አልፈልግም። ይኸውም በፊልም ኢንዱስትሪው ላይ ተሳታፊ ናቸው ተብለው የተጠሩት አካላት በእኔነትና በያገባኛል መንፈስ መሳተፍ አለመቻላቸው ዛሬም እልባት እንዳይገኝ እንቅፋት ይሆናሉ ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም ይህ አይመለከተኝም ስላሉ ነው። ለማንኛውም ወደ ቀደመ ነገሬ ልመለስና ይህ ውይይት የያዛቸውን ቁም ነገሮች በአጭሩ ላስረዳ።
ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ በመምጣት ጥናታቸውን ያቀረቡት የቴአትር ጥበባት፣ ፊልምና ቴሌቪዥን ፕሮዳክሽን ትምህርት ክፍል ኃላፊ ከአቶ ምስጋናው ዓለሙ እንጀምር። የጥናታቸው ርዕስ «የአማርኛ ፊልሞቻችን የባህል መስታወት ወይስ መጋረጃ?» የሚል ሲሆን፤ በዚህ ርዕሰ ጉዳይም በርካታ ቁም ነገሮችን አንስተዋል። ለአብነትም ጥቂቶቹን እናንሳ። ሕንዶች ባህላቸውን ለማካተት ሲሉ በፊልሞቻቸው ታሪክ ውስጥ ሠርግ፣ልደትና ድግስ ብዙዎቹ ላይ አይቀሩም። ምክንያቱም በዚህ ውስጥ አጨፋፈር፣ አዘፋፈንና አለባበሳቸውን ስለሚገለጹ ነው። ጣሊያኖችም ቢሆኑ እንዲሁ በአምስት ዓመቱ ወረራ ጊዜ በርካታ ሲኒማ ቤቶችን ከፍተው ባህልና ፍልስፍናን ለማሰራጨት አመቺ ሁኔታን ሲፈልጉ ነበር።

አሜሪካም እንዲሁ በሆሊውድ ብዙ ነገሯን ሸጣለች። እናም ኢትዮጵያ ከዚህ እሳቤ አኳያ ስትታይ በልጆቿ ከሚሰሩ ፊልሞች ግብር ትሰበስባለች እንጂ ባህሏን በማስተዋወቅ በኩል ተጠቃሚ ነች ማለት አያስደፍርም። ምክንያቱም እስካሁን ድረስ የአሠራር ሥርዓት ያልተዘረጋለት በዘፈቀደና በግለሰቦች ጥረት የሚመራ ስለሆነ ነው። እርግጥ የጸደቀው የፊልም ፖሊሲ ከዚህ በኋላ ለሚከሰቱ ችግሮች እልባት ማግኛ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ይህ የሚሆነው በሚገባ መተግበር ከቻለ እንደሆነ ያስረዳሉ። በፊልም ታሪክ ባህል በአለባበስ፣ አመጋገብ፣ ማህበራዊ መስተጋብር፣ በሙዚቃ ትውፊትና ሌሎችም መንገዶች ይንጸባረቃል። ስለዚህም አልባሳት ዘመን ተናጋሪ፣ ቦታ ጠቋሚ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ደረጃዎችን የሚያመላክቱ መሰራት ይኖርበታል። ይሁንና በፊልም ሥራ ውስጥ አልባሳትን እንኳን ዲዛይን የሚያደርግ ራሱን የቻለ ባለሙያ የለም። ጥናቱ በዳሰሳቸው ፊልሞችም ውስጥ 98 በመቶ የሆነው በዲዛይነሮች ሳይሆን አልባሳት መራጮችና አልባሾች የተሰራ ነው።

የማንኛውም ፊልም ታሪክ አራማጆች እንደሰው ልጅ የሚራቡና የሚጠሙ ገጸ ባህርያት አሏቸው። በተሰጣቸው ዓለም ሲኖሩም እንደ ሰብዓዊነት የሚበላውና የሚጠጣው ምግብና መጠጥ ያስፈልጋቸዋል። አገሪቱ ደግሞ የራሷ ብቻ የሆኑ እንጀራ፣ ጠላና ጠጅ አሏት። ምግብ ፖለቲካ በሆነበት በዚህ ጊዜ የእኛ የምንላቸውን ምን ያክል በታሪኮቻችን ተጠቅመናል ካልን ሃያዎቹን ፊልሞች በአስረጅነት ማየት ተገቢ ነው። ስለሆነም በተዳሰሱት ፊልሞች ውስጥ ከ100 ጊዜ በላይ ምግብና መጠጥ ቀርቧል። ነገር ግን ከምግብ ፒዛና በርገር፣ከመጠጥ ድራፍት በገጸባህርያት ዘንድ እንደሚዘወተሩ ታይቷል።
በተለይ አስቂኝ የፍቅር ፊልሞች ላይ የሚሳሉ ገጸባህርያት የሚመገቡት ፒዛ፣ በርገርና ፓስታ ሲሆን፤ ጭማቂም ይጠቀማሉ። ሲጣሉ ወይም ሲለያዩ ደግሞ አልኮል ጠጭዎች ይሆናሉ። ጉልበት ሠራተኞች እና የኔቢጤዎች ደግሞ ፓስታ በእንጀራ በተዝረከረከ አቀራረብና በመሻማት ይበላሉ። ይህ ደግሞ ምን ያህል ለአገርኛ ምግቦችና መጠጦች ዝቅተኛ አስተሳሰብ እንዳለ የሚያመላክት ነው። ታዳሚውም ይህንን ባህል እንዲያዳብር የሚጋብዝ እንደሚሆንም ያስረዳሉ።በማህበራዊ መስተጋብር ውስጥም ቢሆን የእርስ በእርስ ተግባቦት (ቋንቋ አጠቃቀም፣ የአነጋገር ዘዬዎች፣ ሥነ ቃል፣ ተረትና ምሳሌዎች፣ ሰላምታ አሰጣጥ፣ መረዳጃ ስልቶች (ዕድር፣ዕቁብና ደቦ) እንዲሁም አገራዊ ዳኝነቶች (አፈርሳታ እና በልሃ ልበልሃ) ተጠቃሾች ናቸው። እነዚህ ላይም የሚታየው ይኸው ችግር ነው። ቋንቋ አጠቃ ቀማችን ከርዕስ አሰጣጥ ይጀምራል። አንዳንዱ እንግሊዝኛ፣ አንዳንዱ የውጭ አገር ስም፣ አንዳንዱ ደግሞ ቁጥር ይሆናል። ወደ ንግግሮች ሲገባም ብዙዎቹ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተጽዕኖ ያረፈባቸው ናቸው። አንዳንዶቹ ሆን ተብሎ ቋንቋውን በሚሳሳቱ ጊዜ የሚፈጠርን የሳቅ ምንጭ ታሳቢ ተደርጎ ይዘጋጃሉ።

ፊልሞቻችን እየረሷቸው ከመጡት ጉዳዮች ሰላምታ አሰጣጣችን ሲሆን፤ «ደህና ዋላችሁ፣ደህና አደራችሁ፣እግዚአብሔር/አላህ ይመስገን» መባባል ቀርቶ «ሃይ…ሃይ» ወይም በዝምታ መተላለፍ ተለምዷልም። እርግጥ አልፎ አልፎ ሰላምታ አሰጣጡንም ሆነ መረዳዳቱን በተለይ ትልልቅ ሰዎችና የገጠር ቀረጻ ባለባቸው ፊልሞች ውስጥ እናየዋለን። በደስታና ኀዘን የሚዜሙ ዜማዎችና አካላዊ እንቅስቃሴዎችም ጭምር እንዲሁም የሚያዙና የምንጠቀማቸው የሙዚቃ መሣሪያዎች ከታሪኮቹ ጋር ተስማምተው እንኳን ሲሰራባቸው አይታዩም። ቢካተቱ ኖሮ ግን ተደራስያንን የመያዝ ጉልበት ይኖራቸው ነበርም ሲሉ በጥናታቸው ያነሳሉ። በተካሄደው ናሙናዊ ጥናትም መሠረት ከከተማ እልፍኝ ወጥተው የገጠሩን መንደር የነኩት ፊልሞች በተሻለ መልኩ ባህላዊ እሴቶችን ይዘው ተገኝተዋል፡፡

በአንጻሩ ደግሞ ሙሉ ታሪካቸው አዲስ አበባ ውስጥ ተጀምሮ ያለቀ «ዘመናዊነት» በሚል ሰበብ አገራዊ ለዛቸው ተሸርሽሯል፡፡ 20በመቶ በሚሆን ለዚያውም ያደገበትና የኖረበት ማንነት በገጠሩ የተቃኘ ከውጭ በተሰማና በታየ ማህበራዊ እውነታ መድረኩ ተይዞ የብዙሃኑ ባህል እንዳይከለል ሊታሰብበት እንደሚገባ ያስገነዝባሉ። የፊልም ሙያተኞች የአገራቸውን ባህልና ታሪክ ማወቅ፣ «ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ» ነውና በሙያው ውስጥ ያሉ ፊልም ሰሪዎች፣ ተዋንያን፣ ፕሮዲውሰሮችና በጥቅሉ በዘርፉ የተሰማሩት ሁሉ ለሙያው ክብር መስራት ይኖርባቸዋል ይላሉም። የባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤቶች ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ እሴቶችን ለትውልድ ማሳወቅና ድጋፍ ማድረግ፣ ዘርፉ በፖሊሲ እንዲመራ ማድረግ፣ የትምህርት ተቋማት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥተው መስራት ያስፈልጋልም ሲሉ ይገልጻሉ።ሌላኛው ጥናት አቅራቢ አቶ ስመኝ ሽፈራው በበኩላቸው፤ «እኛ ወዲህ ፊልማችን ወዲያ» በሚል መነሻ ርዕስ ጥናታቸው እንዲህ ይላሉ። ቋንቋዎች የፊልሙ ተመልካች በሆኑት ዘንድ አሉታዊ በሆነ መንገድ ተፅእኖ የመፍጠር ኃይል አላቸው። ስለዚህ አግባብነት ያለው ቋንቋን አለመጠቀም የፊልሙን ባህልና ተፈጥሮአዊነት ይቀይራል። ፊልሞችን በአሁኑ ወቅት የሰለጠነው ዓለም ሾው ቢዝነስ (Show busieness) ብሎ እየሰራው ካለው ሥራ አንጻር ተመልክቶ ቢሰራባቸው አገሪቱ ከሌሎቹ ዘርፎች በተሻለ መልኩ ገቢ የምታገኝበት ይሆን ነበር። ነገር ግን ገና ብዙ መስራት ይጠበቃል።

ብዙ ጎዶሎዎችም አሉበት። ከእነዚህ መካከልም ባለሙያ የሚባሉት ወይንም የሙያው ባለቤት የሆኑት ሰዎች የሙያ ሥነ ምግባር አለማክበር፣ በትምህርት የታገዘ ወይንም እውቀትን ጉልበት ያደረገ የሥራ ውጤት ላይ ያለማተኮር፣ በተለያዩ ሱሶች በመጠመድ አብዛኛዎቹ ማለት ይቻላል ሥራዎችን በባለቤት ስሜት አለመስራት እና በአሰሪ አካል ወይንም በፕሮዲዩስር ላይ የተለያዩ የሥራ ላይ በደሎች እና አላስፈላጊ ወጪዎች መዳረግ፣ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ እና ቦታ የሚፈጸሙ ውሎች እና ስለ ውሎች በቂ የሆነ እውቀት ያለመኖር በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።

ሥራ ከመስራት በፊት በሥራው ላይ በቂ የሆነ ቅድመ ዝግጅት ወይንም ጥናት ያለማድረግ፣ መሠረታዊ የሚባሉ ከሂሳብ ሥራ ጋር የተያያዙ እውቀቶች ያለመኖር እና ሙያውን ለሙያተኛ ያለመተው፣ በሲኒማውም ሆነ በእያንዳንዱ ሥራ መካከል ሥራው እራሱን በቻለ ብልሹ አሠራር ወይንም ሙስና መጠመዱ፣ ስለሚሰሩ ሥራዎች ቀድሞ ጥናት አለማድረግና ሥራዎቹ ከመሰራ ታቸው በፊት ለማን፣ መቼ፣ የት፣ ለምን የሚለውን አለመመለስ እንዲሁም በዘፈቀደ ወይንም በይሆናል ብቻ ወደ ሥራ መግባትም ፊልሞች ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ።በተለይም ገንዘብ ስላለ ብቻ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ የሙያ ባለቤት ስም ተጠሪ ለመሆን የሚደረግ እሸቅድድም ለምሳሌ፡- ተሰጥኦው አቅሙና ችሎታው ሳይኖር ደራሲ፣ ዳይሬክተር፣ ፕሮዳክሽን ማናጀር፣ ፕሮሞተር ወዘተ የሚሉ ሥራዎችን መደራረብ፣ በሥርዓት እንደሌሎች ሙያዎች ሕጋዊ በሆነ ባለሥልጣን የሚሰጡ ማዕረጎች ባለመሆናቸው ሙያውን ባለቤት አልባ የማድረግ ነገሮችም በሰፊው መታየታቸው አንዱ ችግር ነው። በተለይም ተማሪና ጀማሪ ሰዎች እንደልባቸው ልምምድ እንዳያደርጉና በሥራ ላይም ያሉት እንደልብ እንዳይሰሩ መሆኑ ፊልም ትኩረት እንዳያገኝ አድርጓልም ባይ ናቸው።

የቀረፃ ቦታዎች ብዙውን ጊዜ በቦታው ባለቤቶች ፈቃድ ስለሚሆን አዘጋጁ እንደልቡና በፈለገው ሰዓት ቀረጻውን ለማከናወን መቸገሩ እና የፈጠራ ሥራው ላይ ተጽእኖ ማሳደሩም ፈተና እንደሆነ የሚያስረዱት አቶ ስመኝ፤ ጥራት ያለው ፊልም በአገሪቱ እንዳይኖር ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። የይዘት አድሏዊነት የቋንቋ አጠቃቀም ችግር፣ የአንድ ማህበረሰብን ባህል የሚያንቋሽሹ ቃላትን ገለፃዎችን መጠቀም፣ በባህል መገለጫዎች ላይ ተገቢ ያልሆኑ ገለጻዎችን ማቅረብ፣ የባህል መገለጫዎች ትክክል ያልሆኑ አተረጓጎም መስጠትና መሰል ነገሮችም የፊልሙ ኢንዱስትሪ እንዳያንሰራራ እንዳደረገ ይናገራሉ።

በመቶኛ ሲያስቀምጡትም እንዲህ ነበር ያሉት። 75በመቶ የይዘት፣ የአቀራረብ፣ የመረጃ፣ የታሪክ እጥረት ርዕስን በርዕስ፣ የገፀባህሪያት ድርጊት በገፀ ባህሪ መቀየር፣ ቋንቋን በቋንቋ ቦታን በቦታ መለወጥ የተሰራ ሲሆን፤ 90በመቶ ደግሞ የሀሳቡ ምንጭ የፊልሙ አላማ የተወሰደበት ቦታ ግልጽ ያለመሆንነው። በተመሳሳይ ደግሞ ፊልምን የሚያዩ ሰዎች 85በመቶ የሚሆነው አማራጭ መዝናኛ ለማድረግ፣ 10 በመቶው ለፍቅረኞቻቸው ሲሉ፣ አምስት በመቶው ፊልሙን ብለው ፊልሞችን እንደመለከቱት ይሆናሉ። ይህ ደግሞ ፊልምን በፊልምነቱ የሚያየውሰው እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን ያሳያል። እናም በአገሪቱ ያለው ሰው ለፊልም የሚሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑን ከዚህ መረዳት ይቻላልም ነው ያሉት።

በአሁኑ ሰዓት የአገራችን ፊልሞች ከ90በመቶ በላይ የሚሆኑ የፍቅር ኮሜዲ መሠረት አድርገው የሚሰሩ ሲሆኑ፤ ይኸውም የአገር ውስጥ ገበያን ትኩረት በማድረግ የሚሰሩ በመሆናቸው እና ሳይንሳዊና ጥናት ተኮር ከሆነው የፊልም አሠራር ውጪ በሆነ መንገድ የሚመረት መደረጉ በተለያየ መንገድ የፊልም ኢንዱስትሪው ላይ ጫና እያሳረፈ ነው የሚሉት አጥኝው፤ የገንዘብ አቅም፣ የፊልም ሥራ ባለሙያዎች መሠረታዊ የሚባል የፊልም ሥራ እውቀት አለመኖር፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን አለማወቅና የፊልም ፌስቲቫሎች ላይ አለመሳተፉ ለመሳተፉ እንኳን ፍላጎት ቢኖር መረጃው አለመኖር እንደሆነ ያስረዳሉ።ከዓለም አቀፉ ተወዳዳሪነት አንፃርም ሲታይ ግሎባላይዜሽን ወይም ዓለምን በመልካ ምድራዊ አቀማመጧ ምክንያት የተፈጠረውን መራራቅ በመረጃ መረብ በተለይም ሳተላይትን በመጠቀም ወደ አንድ ትንሽ መንደር እንዲሁም አንድ የሆነ በመረጃ በቴክኖሎጂ የተሳሰረ ዘመናዊ ማህበረሰብ መፍጠር አለመቻሉ እንቅፋት እንደሆነ ይጠቅሳሉ። ፊልሞችን በመጠቀም ከባህል ወረራ በተጨማሪ ለተመረቱ ምርቶችና ሽቀጦች ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ሚዲያውንና ፊልሞችን በመጠቀም የገበያ ማፈላለግና ብራንድ በሕዝቦች መካከል የማስረፅን ሁኔታ አለመፍጠሩም እንዲሁ ችግር እንደሆነ ያስቀምጣሉ።

ለዚህም በምክንያትነት የሚያነሱት በቅርቡ በአገሪቱ እየተስፋፉ ያሉ የሳተላይት ስርጭትን በመጠቀም በሚተላለፉ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ላይ በተለይም የውጭ አገር ፕሮግራሞችን ወደኛ ሀገር ቋንቋ በመተርጎም ለሀገራችን ሰዎች ያላቸው ማህበረሰባዊ ፋይዳ ሳይጠና በቀጥታ ተርጉሞ በማቅረብ የቴሌቪዥን ተከታታይ ፕሮግራሞች፣ የቴሌቪዥን ድራማና ሾዎችን ሃሳብ በቀጥታ ኮርጆ በማቅረብ የአገራችን ፊልሞችና ፕሮግራሞች ላይ ቀጥተኛ የሚባል ተፅእኖ መፍጠሩን ነው። ስለሆነም መንግሥት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሊቸረው ይገባል ይላሉ። በዘርፉ ላይ የሚታየውን ከፍተኛ የሆነ ብልሹ አሠራር ወይም ሙስና በልዩ ሁኔታ ከመንግሥት ፈቃድ ሰጪ አካላት ጀምሮ በየደረጃ እስከ ሲኒማ ቤቶች ድረስ ጥናት በማካሄድ የማጥራት ሥራ ሊከናወን ይገባል።

አገሪቱ ካላት እምቅ ባህላዊ፣ ታሪካዊ እና ማህበራዊ እሴት ላይ ያተኮሩ ሥራዎችን በመስራት በዓለም አቀፉ ደረጃ እራሷን የምታስተዋውቅበት ነገር ሰፊ ነው። ይህ ደግሞ ከላይ የተባሉት ተግባራት እውን ሲሆኑ ሊመጣ የሚችል መሆኑ ከግምት ውስጥ አስገብቶ በመስራት ባለሙያዎች በጥናት የታገዘ ማንነትና ባህልን ያለቀቀ እንዲሁም እኛነታችንን ትኩረት ያደረገና ለተቀረው ዓለም የሚያስተዋውቅ ሥራ መስራት አለባቸው ይላሉ። ባለሙያዎች ቢዝነሱን ያተኮረ ብቻ ሳይሆን አገራዊና ማህበረሰባዊ ፋይዳቸው ላቅ ያሉ ሥራዎችን በመስራት የቢዝነስ እና የትኩረት አቅጣጫዎቻቸውን በመቀየር ለዓለም አቀፉ ገበያ የሚበቁ ሥራዎችን መስራት፣ ሚዲያዎች እንዲሁም በዘርፉ ላይ ሂስ የሚሰጡ አካላት ሚዛናዊና ሙያዊ የሆነ ትችት ከማህበረሰቡ ጋር በማያያዝ ለሁሉም ጠቃሚ በሆነ መልኩ ማዘጋጀት አለባቸውም ባይ ናቸው።

ዘርፉ በባለቤትነት የሚያስተዳድረው አካል ወይንም ተጠሪ የሚሆን የሚያስፈልገው እና ምንም ያልተነካ እንዲሁም ሦስቱ የዘርፉ መሠረት በሆኑት ላይ በርካታ ሥራ ቢሠራ በአገር ደረጃ በሰው ኃይል፣ በገቢ፣ በገፅታ ግንባታ ብሎም በአገር ኢኮኖሚ ላይ ጉልህ የሆነ ለውጥ እንደሚመጣ ይታመናል። ስለዚህም የፊልምን ጉልበት ባማከለ መልኩ ሥራዎች እንዲሰሩ መንግሥት ለዘርፉ መተዳደሪያ የሚሆን ሁሉንም ሊገዛ የሚችል ፖሊሲ በሚገባቸው ባለሙያዎች አስጠንቶ ማቅረቡ ጥሩ አማራጭ ነው። እናም ይህንን ተግባራዊ እንዲሆን መታተር ላይ ሊሰራ ይገባል ሲሉም አመላክተዋል።

« በኢትዮጵያ የአማርኛ ፊልሞች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችና የመፍትሄ ሀሳቦች» በሚል ርዕስ ጥናታቸውን ያቀረቡት አቶ ሄኖክ አየለ በበኩላቸው በአጠቃላይ ጉዳዮች ላይ ዳሰሳቸውን አድርገዋል። እናም በዋናነት ምን ምን ጉዳዮችን ዳሰዋል ሲባልም ጥቂቶቹን ላንሳ። የፊልም ሥራ በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ በሁለት እግሩ እንዲቆም ሦስት ዋና ዋና ባለድርሻዎች ያስፈልጉታል ይላሉ። እነዚህም የፊልም ሰሪ፣ የፊልም ሀያሲና ፊልም ተመልካች ሲሆኑ፤ የፊልም ሀያሲ ሥራና ተግባር በተለይ ያልተሰራበትንና ቀዝቃዛ ተሳትፎ የሚታይበት ለመሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚስማሙበት ያስቀምጣሉ። በአሁኑ ሰዓት እንደ ሞያ ሳይሆን እንደ መዋያ እየተቆጠሩ ከመጡ መስኮች መካከል አንዱ የፊልም ሥራ እንደሆነም ይናገራሉ። ለዚህም በምክንያትነት የሚጠቅሱት አንድ ሰው ጋዜጠኛ ገጣሚ፣ ዘፋኝ ፣ የፊልም ባለሙያ ብሎ እራሱን ቢጠራ የሚከለክለው ወይም እውቅና የሚነሳው አለመኖሩ ነው። በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሀሳብና ስሜትን ከመግለፅ ጋር የተያያዙ ሙያዎች ስለሆኑ ማንኛውም ሰው ያለምንም መስፈርት ሀሳቡንም ሆነ ስሜቱን የመግለፅ መብቱ በሕግ የተጠበቀ ስለሆነ፤ ሀሳቡን ለመግለፅ የኮሌጅና የትምህርት ቤት ማረጋገጫ የማቅረብ ግዴታ የለበትም። ይህ ደግሞ ሙያው የሚፈለገው ትኩረት እንዳያገኝ እንዳደረገው ያስረዳሉ።

የባለሙያዎቹ የዕድሜ ክልል በአብዛኛው ከ18 እስከ 35 መሆኑ በፊልሞች ውስጥ ለሚቀረፁ ገፀ ባህሪያት በአብዛኛው ወጣት መሆን፣ የሚነሱ ርዕሰ ጉዳዮችና ጭብጦች በአብዛኛው የወጣቶች ጉዳይ መያዛቸው፣ የእውቀትና የልምድ ማነስ ተጨምሮበት ከ18እስከ 35 ዕድሜ ክልል ያሉ ወጣቶች ከእነሱ አልፈው የታላላቆቻቸውን ፍላጎት ያገናዘበ ፊልም ለመስራት እንዲያስገድዳቸው ማድረጉንና በሕይወት ልምድም የበሰሉ ሰዎች በዋና ዋና የፊልም ሥራ ድርሻዎች ላይ በዝቅተኛ ቁጥር መገኘታቸውን ጨምረው ይጠቅሳሉ። ተመሳሳይ ታሪክ፣ ዘውግ፣ ትወና መስራት፣ ለአዳዲስ ተዋንያን ዕድል አለመስጠት፣ ተመልካችን ዝቅ አድርጎ ማየት፣ ከችሎታ ይልቅ በዝምድና መስራት፣ ያለ ዕውቀት፣ ብቃት በድፍረት መስራት፣ በቂ ቅድመ ዝግጅት አለማድረግ በመከባበርና በመግባባት አለመስራትም እንዲሁ ችግር መሆኑን ያነሳሉ።

«በሲኒማ ቅኝ ያልተገዛ የለም፡፡ አለሁ የሚል ካለ እራሱ ሀሰተኛ ነው፡፡ ከፀጉራችን ስታይል ጀምሮ እስከ ውስጥ ስሜታችንና ምኞታችን ድረስ የቅኝ ተገዥነት ሁኔታ በላያችን ይፀባረቃል» የሚለውን የሀይሌ ገሪማን ሀሳብ ወስደውም እንዲህ ነበር ያሉት አቶ ሄኖክ፤ በፊልም (በሌሎች ኪነ-ጥበብ) ላይ ያለው አቋም ከነባራዊ እውነታ በታች መሆን፣ ቁርጠኝነት፣ የፊልምን ተፅዕኖ አቅምን የመረዳት ሁኔታ፣ የፊልም ጉዳይን ለማስተዳደር ያለ የዕውቀት ክፍተት፣ ተደጋጋሚ የቀረጥና የታክስ ጉዳዮችን የተመለከቱ ጥያቄዎች ምላሽ መንፈግ፣ ፊልምን ከሌሎች የሥራ መስኮች አሳንሶ ማየት፣ በፊልም በሚመለከት የባለሙያዎች ተሳትፎ ማነስ፣ የፊልምን ደካማ ጎን ብቻ ማሳየት በዋናነት ፊልሞች ትኩረት እንዲያጡ እንዳደረጋቸው ያስረዳሉም።ዕውቀት ተብሎ ጥቅም ላይ የሚውለው ሀሳብ ከማንነት ጋር የማይጣጣም የኩረጃ ተፅዕኖ ያለበት መሆን፣ ጠቃሚ ዕውቀት ተብሎ የታመነትንም ሀሳብ በአግባቡ አለመጠቀም በአሁኑ ጊዜ ገንዘብ አቅሙን ያላሳየበት የሥራ መስክ ማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል የሚሉት አቶ ሄኖክ፤ በተለይ እንደ ፊልም ዓይነት የገንዘብ ፍጆታቸው ከፍ ያሉ የሥራ ዓይነቶች ላይ የሚያሳርፈው ተፅዕኖ እጅግ ከባድ እንደሆነ ይናገራሉ። የፊልም ሥራ ይሄን እውነታ ከመረዳት ጀምሮ በየደረጃው መፍትሄ ማበጀት ካልቻለ በጥበብ ላይ መሻሻል ይመጣል ማለት ምኞት ብቻ ይሆናልም ይላሉ። ሥራውን ሰርቶ ተመልካች ጋር ለማድረስ የሚያስፈልግ ገንዘብ ማነስ፣ የተገኘውን ገንዘብ በአግባቡ ያለመጠቀም እራሱን ጥበቡን ገንዘብ የማድረግ ችግርና የጠፋው አቅም ሳይሆን በጎ ፈቃድ ብቻ ነውና በዚህ ላይ አለመሰራቱም እድገቱ በሚፈለገው ደረጃ እንዳያንሰራራ ማድረጉን ይገልጻሉ።

በመጨረሻም «በጎ ፈቃድ የሚጠፋው ሰው እራሱን ለግብረገብ ማስገዛት ወይም የሰው ልጅ ሰብአዊ ባህርይ እየበለፀገ መሄድ ባለመቻሉ ነው፡፡ (ጠና ደዎ 2008 ገፅ 422) » የሚለውን ሀሳብ ይጋራሉ። ስለዚህም ሁሉም ባለድርሻ አካል ሰብዓዊ ባህሪን ተላብሶ ይስራ፤ ባህልን ያሳውቅ በማለት ሀሳባቸውን ቋጭተዋል። በእርግጥ ስለ ፌልም በሌሎች አጥኚዎች ዘንድ በወቅቱ ብዙ ተብሎ ነበር። ነገር ግን ያው እንደሚታወቀው አምዱ ይወስነናልና እስካሁን የተባሉትን በተግባር ለመለወጥ ይጣር ብዬ እኔም ይህንን የመጨረሻ ሀሳባቸውን የሀሳብ መቋጫዬ ላድርግና ልሰናበት። ሰላም!

ጽጌረዳ ጫንያለው
Pages: 1