ሄሎ ሀበሻ ምርጥ የሀበሻ መዝናኛ ሰፈር፣
ይህ ዌብ ሳይት ሀበሻን ከመላው አለም በማገናኘት የሚያወያይ
የሚያዝናና ዌብ ሳይት ወይም መድረክ ነው፥፥
ተሳተፉ ፣ ኮመንት አድርጉ ፣ የራሳችሁን ፃፉ
0 users browsing Airlines. | 1 guest
Pages: 1
Posted on 12-22-17, 08:03 am (rev. 1 by ጮሌው on 12-22-17, 08:04 am)


Karma: 100
Posts: 516/769
Since: 03-20-17

Last post: 242 days
Last view: 242 days
አምሳለ ጓሉ እንደኛነው፣ ካፒቴን
ዋና ዋና ስኬቶች:
በኢትዮጵያ አየር መንገድ ታሪክ፣ የካፒቴንነት ደረጃ ላይ ለመድረስ የበቃች የመጀመርያ ሴት ፓይለት (በ2002 ዓ.ም)
ወቅታዊ ሁኔታ ዋና አብራሪ (ካፒቴን)
የትውልድ ቦታ: ባህርዳር፣ አማራ ክልል፣ ኢትዮጵያ
የትውልድ ዘመን: ህዳር 21 ቀን 1969 ዓ.ም
ወቅታዊ መኖሪያ ስፍራ: አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት
አሳይ የህዝብ ት/ቤት፣ አዲስ አበባ
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት
ቦሌ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት፣ አዲስ አበባ
የዩኒቨርስቲ ትምህርት
ቢኤ፣ (የመጀመርያ ድግሪ) ፣በሥነ ህንፃ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ የቴክኖሎጂ ፋኩልቲ፣ ደቡብ ካምፓስ
የድህረ ምረቃ ትምህርት/ ፖስት ግራጅዌት ዩኒቨርስቲ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአብራሪዎች ማሰልጠኛ
ዋና የስራ ዘርፍ
የአየር መንገድ አብራሪ

የሕይወት ታሪክ

አምሳለ ጉዋሉ፤ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ታሪክ፣ የካፒቴንነት ደረጃ ላይ ለመድረስ የበቃች የመጀመርያ ሴት ፓይለት ናት፡፡ ሴቶች በማይደፍሩትና ወንዶች በእጅጉ በገነኑበት የአብራሪነት ሙያ ውስጥ በመግባት ለሥራው የሚያስፈልገውን ረዥም ስልጠና ከማጠናቀቋም ባሻገር ተከታታይ ጥብቅ ግምገማዎችና ምዘናዎችን በማለፍ ፣ በ2002 ዓ.ም የመጀመርያዋ ሴት ካፒቴን (ዋና አብራሪ) ሆናለች፡፡ እዚህ ደረጃ ላይ ከመድረሷ በፊት ግን ለሰባት ዓመት ተኩል ያህል በልዩ ልዩ አውሮፕላኖች ላይ በረዳት ፓይለትነት ሰርታለች፡፡ 4475 የበረራ ሰዓቶችን በረዳት አብራሪነት ዘመኗ ያስመዘገበችው አምሳለ፤ ካፒቴን ከሆነች ወዲህ ለአንድ ሺ ሰዓታት ገደማ አብርራለች፡፡ አምሳለ ፎከር-50፣ Q-400፣ ቦይንግ 757 እና ቦይንግ 767 በመሳሰሉት አውሮፕላኖች ነውየሰለጠነችውና የሰራችው፡፡ ከእሷ በፊትም ሆነ በኋላ የአብራሪዎች ማሰልጠኛ ገብተው የተማሩ በጣት የሚቆጠሩ ሴቶች ቢኖሩም ወደ ዋና አብራሪነት የሚያደርሰውን ረዥም የሙያ ጉዞ በስኬት በማጠናቀቅ አምሳለ የመጀመርያዋ ናት፡፡ ይሄ ለሰሚ ለተመልካች የሚነሽጥ ታሪኳም ሴቶች ምንም እንደማይሳናቸው በትክክል የሚያሳይ ነው፡፡ ባለትዳርና የሦስት ልጆች እናት ሆና ከቤተሰብሃላፊነት ጋር በሙያዋ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሷ ሲታይ ስኬቷን እፁብ ድንቅ ያደርገዋል፡፡
በ1970 ዓ.ም ባህርዳር ውስጥ አማካይ ገቢ ከነበረው ቤተሰብ የተወለደችው አምሳለ፤ወላጆቿ ካፈሯቸው አራት ልጆች የመጀመርያዋ ናት፡፡ ሦስት ዓመት ሲሆናት ቤተሰቦቿ ወደ አዲስ አበባ ይዘዋት የመጡ ሲሆን የመጀመርያ ደረጃ ትምህርቷን በአሳይ የህዝብ ት/ቤት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ በቦሌ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተከታትላለች፡፡ ወላጆቿ የተማሩ ስለነበሩ፣ ልጆቻቸው ትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩ ከመደገፍና ከማበረታታት ቸል ብለው አያውቁም፡፡

እሷና እህቶቿ ልጆች ሳሉ አባቷ አየርማረፍያ እየወሰዷቸው፣ አውሮፕላን ሲነሳና ሲያርፍ ይመለከቱ ነበር፡፡ ያኔ ነው አውሮፕላን ማብረር የልጅነት ህልሟ ሆኖ በውስጧ የተጠነሰሰው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ሳለች ግን ብልጭ ብሎ የሚጠፋ ምኞት ሳይሆን እርግጠኛ ሆነች፡፡ በ1987 ዓ.ም የዩኒቨርስቲ መግቢያ ብሔራዊ ፈተና በመውሰድ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ የቴክኖሎጂ ፋኩሊቲ ገብታ፣ ሥነ ህንፃ (አርኪቴክቸር) ማጥናት ጀመረች፡፡ ሆኖም የልጅነት ህልሟን አልዘነጋችም፡፡ የአንደኛ ዓመት ተማሪ ሳለች ነው የአብራሪነት ማሰልጠኛ ት/ቤት ለመግባት የመጀመርያ ሙከራዋን ያደረገችው፡፡ ነገር ግን የመግቢያ ፈተናውን በመውደቋ ሙከራዋ ሳይሳካ ቀረ፡፡ ሆኖም ተስፋ አልቆረጠችም፡፡ የህይወት ተመክሮ ስላገኘችበት እንደ ጥሩ አጋጣሚ ነው የቆጠረችው፡፡ አንዳንዴ በህይወት ውስጥ ነገሮች ላይሳኩ ቢችሉም፣ ጨርሶ ተስፋ መቁረጥ እንደሌለባት ጠንቅቃ ታውቃለች፡፡ ወደ አብራሪነት ሙያ የመግባት ሁለተኛ ሙከራዋን ያደረገችው ከአራት ዓመት በኋላ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ግን የበረራ ት/ቤቱን የብቃት መመዘኛ ፈተና ለማለፍ ቻለች፡፡ ከዩኒቨርስቲው እንደተመረቀችም በጥድፊያ ወደ ሥልጠናው ገባች፡፡ ተጣድፋ ብትገባም በዚያው ፍጥነት አልጨረሰችም፡፡ በእሷ ጉድለት ግን አልነበረም፡፡ በወቅቱ በተከሰተው የነዳጅ እጥረት ምክንያት የበረራ ትምህርቱ ከወትሮ የበለጠ ጊዜ ፈጀባት – ከሁለት ዓመት በላይ፡፡ ሥልጠናው ከባድና ፈታኝ ቢሆንም ቅሉ አምሳለ ግን እጅ አልሰጠችም፡፡ በህዳር 1994 ዓ.ም ትምህርቷን በስኬት በማጠናቀቅ በረዳት አብራሪነት ተመረቀች፡፡ ከስምንት ዓመት የበረራ አገልግሎት ጋር የማያቋርጥ ግምገማና ሁሉም ነገሩ እንደ አውሮፕላን የሆነ ዘመናዊ የመለማመጃ ማሽን (ሲሙሌተር ) ላይ የሚደረግ ስልጠናና ምዘና ከወሰደች በኋላ፣ጥቅምት 4 ቀን 2003 ዓ.ም የካፒቴንነት ማዕረግ ለመቀዳጀት በቃች፡፡ አምሳለ፤የቀደምቶቹን ሴት ፓይለቶች እነሙሉመቤት እምሩ፣ አሰገደች አሰፋ፣ ሶፍያ ገዛኸኝ፣ ሃና ወልዴና እሌኒ ታደሰን ፈለግ በመከተል፣ በኢትዮጵያ አቬሽን ታሪክ ስድስተኛዋ ሴት ፓይለት ናት፡፡ በረዳት አብራሪነት የሰሩት ቀደምት ሴት አብራሪዎች ግን ተጨማሪ ሥልጠናና መመዘኛዎችን በማሟላት እንዲሁም እልህ አስጨራሹን ተከታታይ ግምገማ በማለፍ የዋና አብራሪነት ደረጃ ላይ አልደረሱም፡፡

በአገሪቱ የመጀመርያዋ ሴት ካፒቴን መሆን ታሪካዊ ስኬት እንደሆነ ባይካድም ለአምሳለ ግን ትልቁ ኩራቷ የልጅነት ህልሟን አሳክታ የሙያው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለመድረስ መብቃቷ ነው፡፡ ቀድሞውንም ውስጣዊ ብርታት የምታገኘው የመጀመርያዋ ሴት ካፒቴን ለመሆን በነበራት ፍላጎት አልነበረም፡፡ የልጅነት ህልሟን ለማሳካትና በሙያው የላቀ ደረጃ ላይ ለመድረስ ባላት ጥልቅ ፍላጎት እንጂ፡፡
ለአምሳለ ዋና አርአያዎቿ ወላጆቿ ናቸው፡፡ ለዛሬ ስኬቷ እጅግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ታምናለች፡፡ በትምህርቷ እስከ መጨረሻው ድረስ እንድትገፋ በመደገፍ ያበረታቷት ሲሆን ልጆቻቸውን ሁሉ ያሳደጉት “ምንም የማይቻል ነገር የለም” እያሉ ነው፡፡ ሦስት እህትማማቾችና አንድ ወንድም ባለበት ቤተሰባችው ውስጥ የፆታ ጉዳይ ችግር ሆኖ አያውቅም – ሁሉም በእኩል ዓይን ነበር የሚታየው፡፡ ማንነታችንን የሚቀርፀው አካባቢያችን ነው የሚል እምነት ያላት አምሳለ፤ ለስኬት የበቃሁት በተሰጥኦዬና በችሎታዬ ብቻ አይደለም ፣ እንደውም በአብዛኛው የቤተሰብ ድጋፍ ውጤት ነው ትላለች፡፡ ያደገችበትን ማህበረሰብ ውለታም አትዘነጋም፡፡ እንዴት ትዘንጋው? የእያንዳንዱን ቤት ልጅ እድገት እየተከታተሉ “አይዟችሁ በርቱ” የሚሉ ነበሩዋ !
አንዳንዶች ፈተናዎችን እንደውድቀት ቢመለከቱትም ካፒቴን አምሳለ ግን ፈተናዎችን መጋፈጥ የእድገት ሂደት አካልና የጥንካሬ ምንጭ ነው ብላ ታምናለች፡፡ በፆታዋ የተነሳ የአድልዎ ዒላማ መሆኗን፣ በጥርጣሬ መታየቷንና አሉታዊ አስተያየቶችን ማስተናገዷን አትክድም፡፡ ሆኖም እንዲያ ያለው ነቀፌታ ስሜቷን እንዲነካት ፈፅሞ አትፈቅድም፡፡ ህብረተሰብ በሂደት እንጂ በአንድ ጀምበር አይለወጥም ብላ የምታምነው አምሳለ፤ እስከዚያው ግን ቢያንስ በየግላችን ራሳችንን መለወጥ እንችላለን ትላለች፡፡ ከፈተናዎቿ ሁሉ በጣም የከበዳት፣ ሥራዋ የማያፈናፍንና ፋታ የማይሰጥ ከመሆኑ አንፃር ከልጆቿ ጋር የምታሳልፈው በቂ ጊዜ አለማግኘቷ ነው፡፡
አምሳለ ከቤተሰቧ ውጭ ማንን ታደንቂያለሽ ስትባል፣ አቶ ዘውዱ በቀለን ትላለች፡፡ በደማቸው ውስጥ የኤችአይቪ ቫይረስ ያለባቸውን ሰዎች ለመርዳት የተቋቋመውን “ተስፋህ ጎህ” ከመሰረቱት ሰዎች አንዱ የነበረው አቶ ዘውዱ፤ ኤችአይቪ ፖዘቲቭ መሆን የሰው መጠቋቆሚያ ያደርግ በነበረ ጊዜ፣ አደባባይ ወጥቶ ኤችአይቪ እንዳለበት በድፍረት የገለፀ ፈርቀዳጅ ግለሰብ ነበር፡፡ በበሽታው ዙርያ ግንዛቤ በመፍጠር ኤችአይቪ ፖዘቲቭ የሆኑ በርካታ ሰዎች፣ እውነታውን ተቀብለው ከበሽታው ጋር እንዲኖሩ አግዟል፡፡ አምሳለ የምታደንቀውም ለዚህ ነው – የበርካቶችን ህይወት ለመታደግ የላቀ አስተዋፅኦ በማበርከቱ፡፡
ካፒቴን አምሳለ፤ የስኬት ታሪኳን ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች፣ በተለይ ለወጣት ሴት ተማሪዎች በማጋራት ለወገኖቿ የድርሻዋን እያበረከተች ነው፡፡ በአዲስ አበባና ሌሎች ክልሎች ልዩ ልዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በሚያሰናዷቸው ዝግጅቶች ላይ እየተጋበዘች፣ የህይወት ታሪኳንና ተመክሮዋን ለአዲሱ ትውልድ በማካፈል፣ ወጣቶች በህልሞቻቸው እንዲተማመኑ በማበረታታትና በማነቃቃት እያገዘች ነው፡፡

ወደፊት አምሳለ እስካሁን ያላበረረቻቸውን ቦይንግ 777 እና 787 ን ጨምሮ ሌሎች አውሮፕላኖችን ማብረር ለመማር ታስባለች፡፡ በአብራሪነት ሙያዋ በመግፋትም የልጅነት ህልሟን በእውን እየኖረች የመቀጠል እቅድ አላት፡፡ በቤተሰብ ህይወቷ ደግሞ ልጆቿ ስኬታማ ሆነው ማየት ትሻለች፡፡ ስኬታማ ለመሆን የሚያስችላቸውን ጥሩ ትምህርት እያገኙ መሰረት እንዲይዙላት ትመኛለች፡፡ ለኢትዮጵያ የምታልመው – ከድህነት የተላቀቀች፣ ሰዎች ተግባብተውና ተስማምተው የሚኖሩባት፣ ያለ ፆታ ልዩነትወንዱም ሴቱም እኩል እድል የሚያገኙባት አገር ሆና ማየት ነው፡፡
ካፒቴን አምሳለ፤ በዛሬው ዘመን በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚያድጉ ልጃገረዶችና ሴቶች የምትለግሰው ምክር እንዲህ የሚል ነው –
ምንጊዜም በህይወታችሁ ውስጥ ቅድምያ የምትሰጡትን ነገር ለይታችሁ ማወቅ አለባችሁ፡፡ በወጣትነታችሁ ከሁሉም በፊት ለትምህርታችሁ ቅድምያ ስጡ፡፡
ላለማችሁት ነገር በሙሉ ልብና ቁርጠኝነት ትጉ፡፡ ጨርሶ ተስፋ አትቁረጡ፡፡
የልባችሁን ፍላጎት ለይታችሁ እወቁ፡፡ የመረጣችሁት ሙያ ወንዶች የገነኑበት ቢሆንም እንኳ ደፍራችሁ ግቡበት፤ ግነኑበት፡፡
ዋና የመረጃ ምንጮች
ከካፒቴን አምሳለ ጓሉ ጋር የተደረገ ቃለምልልስ
አጥኚ
ምንትዋብ አፈወርቅPages: 1