ሄሎ ሀበሻ ምርጥ የሀበሻ መዝናኛ ሰፈር፣
ይህ ዌብ ሳይት ሀበሻን ከመላው አለም በማገናኘት የሚያወያይ
የሚያዝናና ዌብ ሳይት ወይም መድረክ ነው፥፥
ተሳተፉ ፣ ኮመንት አድርጉ ፣ የራሳችሁን ፃፉ
0 users browsing Travel - ጉዞ. | 1 guest
Pages: 1
Posted on 12-01-17, 08:10 pm (rev. 1 by Ye Arada Lij on 12-01-17, 08:14 pm)


Karma: 90
Posts: 637/887
Since: 02-29-16

Last post: 373 days
Last view: 373 days
እንዴት ናችሁ? የታክሲ፣ የአንበሳ ባስ፣ የሀይገር፣ የባቡር ተሳፋሪዎች? ሁሉ ነገር አማን ነው? ቆይ ግን እናንተ እስከመቼ ድረስ ነው እንዲህ ለታክሲና ለባስ ተሰልፋችሁ? እንዴ! እስከመቼ ነው ባቡር ውስጥ የምትጋፉት? የአገር አቋራጭ አውቶብስ ተሳፋሪዎች ግን አይደብራችሁም ቀኑን ሙሉ በመኪና ስትሄዱ ስትውሉ? ለምን በአውሮፕላን አትሄዱም? ሃሃሃሃሃ … «እርሟን ብታፈላ …» አለች አያቴ፡፡

የዛሬ የጉዞ ማስታዎሻዬ እስካዛሬ ከነበረው ለየት ሊልላችሁ ነው፡፡ ታዲያ እስከመቼ የታክሲ ሰልፍ እንደዘገብኩ እኖራለሁ፤ አንዳንድ ቀን እንኳን የአውሮፕላን የጉዞ ማስታወሻ ልጻፍ እንጂ፡፡ እንደሚታወቀው በአገር አቋራጭ አውቶቡስ መሄድ የጉዞ ማስታወሻ ለመጻፍ ምቹ ነው፡፡ «በመስኮቱ አሻግሬ ሳይ …» እያሉ ለመተረክ ያመቻል፡፡ በአውሮፕላን ብትሄድ ግን በመስኮቱ የሚታይህ የተጠቀጠቀ ደመና ብቻ ነው፡፡ በእርግጥ ልብ ብሎ ላስተዋለ ደመናው የሚፈጥራቸው ቅርጾች እንኳን አንድ የጉዞ ማስታወሻ አንድ የሥዕል ጋለሪ ይወጣቸዋል፡፡ ምን ዋጋ አለው ይሄ የሥዕል ጥበብን ይጠይቃል፡፡

ለማንኛውም በአውሮፕላን በመሄዴ የጉዞ ማስታወሻ ላይ የሀሳብ እጥረት አላጋጠመኝም፤ እንዲያውም በጣም ነው የበዛብኝ፡፡ በእርግጥ ጉዞው የ45 ደቂቃ ነው፡፡ ስለዚህ ጉዞ ማስታወሻው ዋናው አካል በአውሮፕላኑ ውስጥ ያለው ቆይታ ሳይሆን በአየር ማረፊያዎች ውስጥ ያለው ቆይታ ይሆናል፡፡ አቤት ፍተሻ! አሁን እኔን ምን ይይዛል ብለው ነው?

የጉዞ ማስታወሻውን ከአውሮፕላኑ ይልቅ «የቦሌ ቆይታዬ» ብለው ይሻል ነበር፡፡ እንዲያውም በጣም ከመማረሬ የተነሳ «አንበሳ ባስ ማረኝ» ብዬ ነበር፡፡ ፍተሻ የለ፣ «አደጋ የደረሰ እንደሆነ እንዲህ አድርጉ» የሚል ማስፈራሪያ የለ፣ ጫማ ማውለቅና ማጥለቅ የለ ዝም ብሎ መግባት እኮ ነው፡፡ምሽት 1፡25 ለሚጀመረው ጉዞ 10፡00 ተገኘን፡፡ በእርግጥ እዚህ ላይ አንድ ነገር ተገነዘብኩ፡፡ እኔ ምንም ዕቃ ስለሌለኝ እንጂ ትልልቅ ሻንጣ ለያዙ ሰዎች እንዲያውም ሲያንሳቸው ነው፡፡ እንኳን ለእነርሱ ለኔም ረጅም ጊዜ ወሰደ፡፡ በመጀመሪያ 10፡00 መገኘት እንዳለብኝ ሲነገረኝ ‹‹እንዲህ ከሆነ በመኪና አልሄድም እንዴ!›› እያልኩ ተቆጥቼ ነበር፡፡ ከገባሁ በኋላ ነው ነገሩ የገባኝ፡፡


አውሮፕላኑ ያለበት ቦታ ላይ ለመድረስ ሁለት የፍተሻ ቦታዎች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ፍተሻ ተጀመረ፡፡ ባለትልልቅ ሻንጣ ረጅም ሰልፍ ተሰልፎ የያዘውን ዕቃ ያስመዘግባል፡፡ እንኳንም ምንም ዕቃ የለኝ እያልኩ የያዝኳትን ቦርሳ የዕቃ ማሳለፊያው ላይ ወርውሬ ቆም አልኩ፡፡ በሆነች ቀጭንዬ መተላለፊያ ውስጥ አዳሜ ጫማውን እያወለቀ ያልፋል፡፡ ይሄ ነገር የሃይማኖት ቦታ ነው እንዴ እያልኩ እኔም አወለቅኩ፡፡ ከበሩ ላይ ቆም እንዳልኩ ተቆጣጣሪው እለፍ የሚል ምልክት አሳየኝ፤ ላልፍ ስል ምናባቱ እንደሆነ አላውቅም በሩ ጮኸብኝ፡፡

«ምን ይዘሃል አለኝ?» ሰውዬው፤ «ኧረ ምንም አልያዝኩም» ብዬ ድርቅ እኔ ደግሞ! በል ተመለስ፡፡ «እንዴ! ጓደኞቼ እየሄዱ ለምንድነው እኔ እምመለሰው» ስለው «‹እሺ ቀበቶህን ፈተሃል?» «አልፈታሁም!» «በል ቀበቶህንም፣ የእጅ ሰዓትህንም፣ ቀለበትህንም ፍታና ግባ» አለኝ፡፡ የዚህን ጊዜ ቆፍጠን አልኩና «የምን ቀለበት ነው እጄ ላይ ያየኸው?» አልኩት ተናድጄ፡፡ ምክንያቱም ከኋላየ አንዲት ቆንጂዬ ልጅ ስለነበረች ለመጀናጀን ዝግጅት ላይ እያለሁ ይህን በማለቱ ተናድጃለሁ፡፡ «አይ ቀለበት ካለህ ነው ያልኩህ» አለኝ፡፡ እንደገና ወደኋላ ተመልሼ ቀበቶዬን፣ ሰዓቴን ፈታሁኝ ገባሁ፡፡ አሁን ከጮኸ ይሄ በራችሁ እልም ያለ ቀጣፊ ነው ብየ ልገላምጥ ስዘጋጅ ለካ እሱ ሀቀኛ ነው ዝም አለኝና አለፍኩ፡፡

በሩን አልፎ በማሽን ውስጥ አልፈው የሚመጡ ዕቃዎቼን መጠባበቅ ጀመርኩ፡፡ ቀበቶዬ መጣ፤ እሱን አነሳሁ፤ ሰዓቴ መጣ እሱንም አነሳሁ፡፡ ጫማዬን ስጠባበቅ ግን አንድ ነገር ተፈጠረ፡፡ ከተቀመጠበት ሳህን ላይ ወድቆ ነው ለካ አንዱ ጫማዬ ቀርቶ አንዱ መጣ፡፡ በድንጋጤ «አንዱ ጫማዬስ!» ስል ለነገሩ አዲስ መሆኔን ማን እንደነገረው አላውቅም ተቆጣጣሪው «አይ ጉድ! በቃ እዚህ ውስጥ ከገባ አይገኝም አትጠብቅ አለኝ» እንዴት እንደተናደድኩ! እስኪ አስቡት ለመጀመሪያ ጊዜ በአውሮፕላን ስሄድ በአንድ እግር ጫማ፤ በቃ ይሄኛውንም ልጣለውና በባዶ እግሬ ልሁን እያልኩ ስወዛገብ የተቆጣጣሪው ፈገግታ ቀልዱን እንደሆነ ነገረኝ፡፡ ወዲያውኑም ጫማዬ ከሌሎች ሰዎች ዕቃ ጋር መጣ፡፡ ፐ! ብድግ አድርጌ ልስመው ምንም አልቀረኝም ነበር፡፡


ወደ ቀጣዩ የፍተሻ ቦታ ስንሄድ ግን ብዙ ዘዴ መጣልኝ (ከስህተት መማር ማለት እንዲህ ነው)፡፡ የእጅ ሰዓቴን፣ ቀበቶዬን፣ የኪስ ቦርሳዬን ሁሉ እያወጣሁ ቦርሳዬ ውስጥ ከተትኳቸው፡፡ አሁን የቀረኝ ጫማ ብቻ ነው፡፡ የዕቃ ማሳለፊያው ላይ ቦርሳዬንና ጫማዬን ብቻ ጣልኩ፡፡ ይሄ በር አሁንስ ምናባቱ ይል ይሆን ብዬ በኩራት እየተጀነንኩ በውስጥ አለፍኩ፡፡ ምንም ሳይናገረኝ ከወዲያኛው ወለል ተገኘሁ፡፡ ጫማዬንና ቦርሳዬን ብቻ አንስቼ ግልግል!

አሁን የፍተሻው ነገር አልቋል፡፡ ከመጠባበቂያ ቦታው ላይ ደርሻለሁ፡፡ ከጣሪያው ላይ ባለው ማይክራፎን በግልጽ የማትሰማ ሴት በአማርኛና በእንግሊዝኛ ታወራለች፡፡ እንግሊዘኛ ውንስ አቅቶኝ ነው ልበል እንዴት አማርኛው አይሰማኝም? ይህ የሆነው አንድም ስታወራ ታፈጥናለች፤ እንድም የስፒከሩ ድምጽ ችግር አለበት፡፡ በነገራችን ላይ በእንዲህ አይነት ቦታዎች ላይ መልዕክት የሚናገሩ ሰዎች ላይ ብዙ ቅሬታ ሰምቻለሁ፡፡ ለምሳሌ አውቶቡስ ተራ ውስጥ መልዕክት የሚያስተላልፉ ሰዎች ምን እንደሚሉ አይታወቅም፡፡ እያንዳንዷን ቃላት ለይቶ መጥራት ሲገባቸው ዝም ብለው ትትትትትት ማለት ብቻ ነው (እንደ ታክሲ ረዳቶች ማለት ነው)፡፡
ለማንኛውም እንደምንም እያልኩ ስሰማት የምትናገረው ተረኛ ተጓዦችን ነው፡፡ የአውሮፕላኑን ቁጥር የሚሄዱበትን ቦታ እየጠራች እንዲሄዱ ታዝዛለች፡፡ እኔም የምበርበት አውሮፕላን ተራ ደረሰና ወደ አውሮፕላኑም ሄድኩ፡፡

የአውሮፕላኑ በር ላይ አንዲት ቆንጅዬ ልጅ ቆማ የሚገቡትን ሰላም ትላለች፡፡ ታክሲ ውስጥ ሰላም እያልኳቸው እምቢ ብለውኝ ተስፋ የቆረጥኩትን እዚህ ደግሞ ራሷ ሰላም ትላለች እንዴ ብዬ ገረመኝ፡፡ ልጅቷን ሰላም ለማለት በጣም ከመቸኮሌ የተነሳ ከፊቴ ያሉት ሰዎች አናደዱኝ፡፡ እንደምንም ተራው ደረሰኝ፡፡ አይ አለመታደል! ልክ እኔ ጋ ስደርስ አንድ ጨቅጫቃ ሰውዬ ቦርሳ ሊያስቀምጥ «የአውሮፕላኑን ኪስ ክፈችልኝ» አላት፡፡ «ምናባክ ራስህ አትከፍተውም እንዴ!» ልለው አስቤ ሳስበው ጠብ ፈጠርክ ብለው ከአውሮፕላኑ ቢያስወርዱኝ ይህ ብርቅ ጉዞዬ ሊሰረዝብኝ ሆነ፡፡ ሰውየውን በሆዴ ረግሜ የወንበር ቁጥሬን ፈልጌ ተቀመጥኩ፡፡


ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ የአውሮፕላኑ በር ተዘጋ፤ ጉዞው ሊጀመር ነው፡፡ ያቺ በሩ ላይ ቆማ ሰላም ስትል የነበርችዋ ልጅ የስልክ እጀታ አንስታ ማውራት ጀመረች፡፡ በመጀመሪያ የካፒቴኑን ስም ተናገረች፡፡ ቀጥላ የምንሄድበትን ቦታ፣ የመነሻ ሰዓታችንን፣ የመድረሻ ሰዓታችንን… እያለች ተናገረች፡፡ ቆይ ግን መነሻውስ ይታወቅ መድረሻውን እንዴት እርግጠኛ ሆነች? ደግሞ እኮ አንድም ደቂቃ አልተዛባባትም፡፡

አውሮፕላኑ ተነሳ፤ መሬቱን ለቆ በአየር ላይ መብረር ጀመረ፡፡ ልጅቷ አሁንም የስልኩን እጄታ አነሳች፡፡ ከመሬት ምን ያህል ጫማ ከፍታ ላይ እንዳለን፣ የምንሄድበትን ከተማ የአየር ንብረት ተናገረች፡፡ አደጋ ቢፈጠር እንኳን ምን ማድረግ እንዳለብን ተናገረች፡፡ ይህኔ ነበር ባር ባር ያለኝ፡፡

አውሮፕላኑ ገና እንደተነሳ አዲስ አበባን ቁልቁል አየኋት፡፡ አቤት ስታምር! እነዚያ አንጋጥጬ የማያቸው ትልልቅ ህንጻዎች እኔን አንጋጠው የሚያዩኝ መሰለኝ፡፡ በጎዳናዎችና ህንጻዎች ላይ ያሉት መብራቶች በመሬት ላይ በትንንሹ የተረጩ ይመስላሉ፡፡ የአዲስ አበባን የምሽት ውበት እያጣጣምኩ ወዲያውኑ የአውሮፕላኑ ከፍታ ምንም ነገር እንዳላይ አደረገኝ፡፡

ከጥቂት ደቂቃ በረራ በኋላ ያቺ ሰላምታዋ ያለፈኝ ልጅ የሚበላና የሚጠጣ ነገር ይዛ መጣች፡፡ ይህኔ ነው ማዋራት፡፡ የሚበላው አንድ አይነት ስለሆነ እሱን ከሰጠችኝ በኋላ የሚጠጣውን «ምን ይሁንልህ?» አለችኝ፡፡ እኔም ለማዋራት ብዬ የታሸጉትን ምን ምን እንደሚባሉ ጠየቅኳት (በእርግጥ ስለማላውቀውም ነው) በኋላ ስትነግረኝ ግን ስለታሸገ እንጂ ሁሉም የማውቃቸው የጁስ አይነቶች ነበሩ፡፡ አንዱን ተቀበልኩና ጠጣሁ፡፡

አሁን ማረፊያችን ሊደርስ ነው፡፡ እንደተለመደው የስልክ እጀታዋን አንስታ የካፒቴኑን ስም፣ የአየር ሁኔታውን፣ ያረፍንበትን ከተማ (እያወቅነው እኮ ነው) ነገረችን፡፡ የሮቢላው ጉዞ ተጠናቀቀ፡፡

ሮቢላ ማለት ልጅ እያለሁ አውሮፕላንን እጠራበት የነበረው ስም ነው፡፡ በሰማይ ላይ ሲሄድ ስናየው ከጓደኞቼ ጋር ሆኜ ‹‹ሮቢላ ና ውሰደኝ እንል ነበር›› ለመሆኑ ያንን ሰምቶኝ ይሆን? ethpress | ዋለልኝ አየለ
Pages: 1