ሄሎ ሀበሻ ምርጥ የሀበሻ መዝናኛ ሰፈር፣
ይህ ዌብ ሳይት ሀበሻን ከመላው አለም በማገናኘት የሚያወያይ
የሚያዝናና ዌብ ሳይት ወይም መድረክ ነው፥፥
ተሳተፉ ፣ ኮመንት አድርጉ ፣ የራሳችሁን ፃፉ
0 users browsing Education - ትምህርት. | 1 guest
Pages: 1
Posted on 11-14-17, 07:51 am


Karma: 90
Posts: 619/887
Since: 02-29-16

Last post: 373 days
Last view: 373 days
አተም
አተም ማለት የአንድ ንጥረነገር አነስተኛው ክፍል ነው፤
በመዋቅር ደረጃ አተም፣ እንደ ማዕከል ከሚያገለግል አስኳል
(ኒዩክለስ) እና በዚያ ዙሪያ ከሚዞሩ ኤሌክትሮኖች የተመሰረተ
ነው፤ አስኳል(ኒዩክለስ) በራሱ፣ ከሌሎች ማለትም ኒዩትሮን እና
ፕሮቶን ከተባሉ ደቂቅ አካሎች የተሰራ ነው፡፡ በኒኩለስ ውስጥ
የሚገኘው የነኝህ ደቂቅ አካላት ብዛት አንድ ቁስ ብረት ይሁን
ወርቅ፣ ወይም ሌላ ክስተ ነገር የሚለውን የሚወስን ነው፡፡
የኬሚካል ንጥረነገሮች (periodic table) ቅደም ተከተላዊ
ገበታ የተዘጋጀው በነኝህ ቁጥሮች ብዛት ላይ በመመስረት ነው፤
ለምሳሌ በገበታው ላይ በአንደኝነት የሚገኘው ሃይድሮጅን
የተባለው ንጥረነገር ሲሆን፣ የሃይድሮጅን አተም ኒዩክለስ
የተመሰረተው ከአንድ ፕሮቶን ብቻ ነው፤ ነገር ግን በገበታው
ላይ በቅደም ተከተል ስንመለከት በተፈጥሮ ከሚገኙት ውስጥ
ትልቅ ኒዩክለስ ያለውና ጨረራ አመንጪ የሆነውን የዩራንየም
አተም እናገኛለን፤ በዚህ አተም ኒዩክለስ ውስጥ ያሉት የደቂቆች
(particles) ብዛት 238 ነው፤ ማለትም 92 ፕሮቶን ሲደመር
146 ኒዩትሮን ነው፤ በርግጥ አይሶቶፕ የሚባል ሌላም ባሕሪ
አለው፡፡ አንድ አተም ምንጊዜም እኩል የኤሌክትሮኖች(አሉታዊ)
እና ፕሮቶኖች(አዎንታዊ) ቁጥር አለው፡፡
ቻርጅ(ሙሊት)
ቻርጅ(ሙሊት) ማለት አዎንታዊ(ፓዘቲቭ) ወይም አሉታዊ
(ኔጌቲቭ) የቁስ አካል ባህሪይ ነው፤ አንድ አካል አዎንታዊ ቻርጅ
የሚኖረው በአካሉ ላይ ያሉት ፕሮቶኖች ከኤሌክትሮኖች
ሲበልጡ ሲሆን፣ በአንፃሩ ደግሞ አንድ አካል አሉታዊ ቻርጅ
የሚኖረው በአካሉ ላይ ያሉት ኤሌክትሮኖች ቁጥራቸው
ከፕሮቶኖች ሲበልጡ ነው፡፡
ግልል(ኒዩትራል)
አዎንታዊ(ፓዘቲቭ) እና አሉታዊ(ኔጌቲቭ) ቻርጆች እኩል
የሆኑበት ሁኔታ ወይም አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ቻርጅ ያለመኖር
ባህሪይ ነው፡፡
እስታቲካ ኤሌትሪክነት(static electricity)
እስታቲካ ኤሌትሪክነት የሚፈጠረው ሁለት የተለያዩ ቁሶች
የመፋተግና የመነካካት ሁኔታ ሲኖራቸው ነው፤ ማንኛውም ቁስ
ከአተሞች እንደተሰሩ እናውቃለን፤ አተሞች ደግሞ የኤሌክትሪክ
ሙሌት ያላቸው ናቸው፤ ምድራችን እንዲሁም ሁለንተናዊው
ዓለም በአንድ አተም አስኳል ዙሪያ በሚዞሩ አሉታዊ ደቂቆች
(ኤሌክትሮን/ነጌቲቭ) እና በአስኳል ውስጥ በሚገኙ አዎንታዊ
ደቂቆች (ፕሮቶኖች/ፓዘቲፍ) ምጥጥን የተመሰረተ ነው፡፡
እስታቲካ ኤሌትሪክነት ማለት ሚዛኑን ያልጠበቀ የኤሌክትሪክ
ሙሌት በአንድ ቁስ ውስጥ ወይም ወለል ላይ መኖር ማለት
ነው፤ ይህንን ስንል አዎንታዊ ወይም አሉታዊ የሆነ ማለት ነው፤
ይህ ሚዛኑን ያልጠበቀ የኤሌክትሪክ ሙሌት(charge)፣
በኤሌክትሪክ ዥረት(ከረንት) ወይም በኤሌክትሪክ አስተላላፊ
ቁስ ጋር በሚኖር ንክኪ በስደት ወደ ሌላ አካል እንዲተላለፍ
(ዲስቻርጅ) ካልተደረገ፣ በዛ ቁስ ላይ ሚዛኑን እንዳልጠበቀ
ሆኖ ይቆያል፡፡ የእስታቲካ ኤሌትሪክ ሙሌት ማንኛውም ሁለት
ቁሶች ተነካክተው ሲለያዩ ይፈጠራል፤ ምክንያቱም ከሁለቱ ቁሶች
ቢያንስ አንደኛው ለኤሌክትሪክ ዥረት ከፍተኛ የሆነ ተቃውሞ
(ሪዚስታንስ) ይኖረዋል፤ በመሆኑም የኤሌክትሪክ ፍሰትን
የመክላት ባሕሪ ይኖረዋል፡፡
ይህ በአንድ ቁስ ላይ የኤሌክትሪክ ሙሊቱን ሚዛን ሳይጠብቅ
የሚገኝ ክስተ ሁኔታ በሰዎች ላይ የሚያደርሰውን ተፅእኖ
አብዛኞቻችን በተለያየ አጋጣሚ የምናውቀው ነው፤ ምክንያቱም
አንዳች እቃ ስንነካ የንዝረት ስሜቱን እንሰማለን፣ “ጣ” የሚልም
ድምፅ እንሰማለን፤ አልፎ ተርፎም በምሽት እሳት ሲፈነጥቅ ሁሉ
እናያለን፤ እነኝህ ሁኔታዎች የሚፈጠሩት ተከማችቶ የሚገኘው
የኤሌክትሪክ ሙሌት እንደ ብረት ያሉ የኤሌክትሪክ ዥረትን
በከፍተኛ ደረጃ ወደ መሬት የሚያስተላልፉ ቁሶች ሲያገኝ ግልል
(ኒዩትራል) ለመፍጠር የሚያስችል መሰደድ ሲያጋጥም ነው፡፡
በመሆኑም ብረት ነክ ቁስ ስንነካ የሚያጋጥመን ንዝረትና
ክውታው በሁለት በተነካኩ ነገሮች መካከል የቻርጆች ግልልነት
(ኒዩትራላይዜሽን) ሲፈጠር ነው፡፡
የእስታቲካ ኤሌትሪክ ሙሌት እንዴት ይፈጠራል?
ማንኛውም ቁስ ከአተሞች እንደተሰራና አተሞችም የኤሌክትሪክ
ግልል(ኒዩትራል) ያላቸው እንደሆነ እናውቃለን፤ ምክንያቱም
አሉታዊና አዎንታዊ ሙሊታቸው እኩል ስለሚሆንና ሚዛኑን
ስለሚጠብቅ፤ ይሁንና ሁለት የተለያዩ ቁሶች ሲነካኩ አሉታዊ
ቻርጆች(ኤሌክትሮንስ) ከአንደኛው ቁስ ወደ ሌላኛው መሰደድ
ያጋጥማቸዋል፤ ይህ ሁኔታ በሁለቱም ቁሶች ላይ ሚዛንን
የሚያሳጣ ይሆናል፤ ምክንያቱም ኤሌክትሮኖች የተሰደዱበት ቁስ
ፓዘቲቭ(አዎንታዊ) ሙሌት ይሆናል፤ አሉታዊ(ኔጌቲቭ) ቻርጆችን
የተቀበለው ቁስ ደግሞ ኔጌቲቭ(አሉታዊ) ሙሌት ይሆናል፤
እነኝህ ሁለት ቁሶች ሲነካኩ የተከሰተው የሙሊት ዝንፈት ቁሶቹ
ከተላቀቁም በኋላ አብሯቸው ይቆያል፤ በተለይ ሁለቱም ቁሶች
ኮረንቲ አስተላላፊ ካልሆኑ አብሯቸው ይቆያል፡፡
ቁሶቹ ኤሌክትሪክ አስተላላፊ ከሆኑ ሙሊታቸው የመባከን ሁኔታ
ስለሚያጋጥመው የእስታቲካ ኤሌትሪክ የመከማቸት ሁኔታ
ስለማይኖር፣ ቁሶቹ ንዝረት ወይም ክውታውን የመፍጠር
ሁኔታቸው ዝቅተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁንና ቁሶቹ ኮረንቲ
የማያስተላልፉ ከሆኑ፣ እንዲሁም በንክኪ ወደ አንዳች ቁስ
የሚያስተላልፉበት ሁኔታ ከሌለ፣ ሙሊታቸውን ይዘው ይቆያሉ፤
ሲነኩም የንዝረት ሁኔታው ከፍተኛ ይሆናል፡፡
የሚቀርቡ የተለያዩ ጥያቄዎች
የበራችንን እጀታ ስነካ ለምን ይነዝረኛል? ማንኛውንም ብረት ነክ
ዕቃ ስነካ ለምን ይነዝረኛል?
አብዛኛውን የምንጫማቸው ጫማዎች ኤሌክትሪክን
የማያስተላልፉ የፕላስቲክ ሶል አላቸው፤ በቤትም ሆነ በሌላ
አካባቢዎች ስንራመድ የሚኖረው ሰበቃ በጫማችን ሶል ላይ
የእስታቲካ ኤሌትሪክ ሙሌት እንዲከማች ያደርጋል፤ ይህ ሁኔታ
በተለይ የምንራመድበት ወለል ራሱ ኤሌክትሪክ አስተላላፊ
ካልሆነ ሁኔታውን የሚጨምር ነው፤ በተለይ በቤቶች ውስጥ
ከሆንን ደግሞ ምንጣፎች ሁኔታውን የበለጠ እንዲከማች
የሚያደርጉ ናቸው፡፡
በጫማችን ሶል ላይ የሚፈጠረው የእስታቲካ ኤሌትሪክ ሙሌት
ወደ ሰውነታችን የእስታቲካ ኤሌትሪክ ስርፀት እንዲኖር ያደርጋል፤
ይህ ሙሌት ከፍተኛ ቮልቴጅ እንዲኖር ያደርጋል፤ በመሆኑም
በዚህ ሁኔታ ላይ እያለን ኤሌክትሪክ አስተላላፊ ቁስ በምንነካበት
ወቅት ይህ የተከማቸ የእስታቲካ ኤሌትሪክ ሙሌት በአንድ ጊዜ
ወደ አስተላላፊው አካል ይሰደዳል፤ በዚህ ጊዜ ከፍተኛ የሆነ
ንዝረት ይሰማናል፡፡ ይህን ሁኔታ በቤት ውስጥ በጫማ
በመንቀሳቀስና በባዶ እግር በመንቀሳቀስ የራሳችንን ሙከራ
በማድረግ ማየትና ማረጋገጥ እንችላለን፤ በባዶ እግራችን
ከተንቀሳቀስን የእስታቲካ ኤሌትሪክ ስለማይከማች እቃዎችን
ስንነካ ንዝረት አይኖርም፡፡
ወንበር ላይ ቁጭ ብለን፣ ሳንራመድስ ንዝረቱ ለምን
ያጋጥመናል?
በወንበር ላይ ቁጭ ስንል፣ በወንበሩና በልብሳችን መካከል
የሚኖረው መፋተግና መተሻሸት፣ ከፍተኛ የሆነ የእስታቲካ
ኤሌትሪክ ሙሌት በልብሳችን ላይ እንዲከማች ሊያደርግ
ይችላል፤ ወንበሩ ላይ ቁጭ ብለን እያለ በሰውነታችን ላይ
የሚኖር ቮልቴጅ ዝቅተኛ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ከወንበሩ
ስንነሳ በላያችን ላይ የተከማቸው የእስታቲካ ኤሌትሪክ ሙሌት
አብሮን ይነሳል፤ በዚህ ጊዜ የሰውነታችን ቮልቴጅ በፍጥነት
ከፍተኛ ይሆናል፤ ምክንያቱም ተቃራኒ ከሆነ የቻርጅ ሙሊት ጋር
ስለምንለያይ ማለት ነው፤ በመሆኑም በዚህ ሁኔታ ላይ ሰዎችን
ብንጨብጥ በላያችን ላይ የተከማቸ የእስታቲካ ኤሌትሪክ ከኛ
ወደ ሌሎች መሰደድ ስለሚያጋጥም ከፍተኛ ንዝረት ሊሰማን
ይችላል፡፡
አብረውን ያሉ ሌሎች ሰዎች ሳይነዝራቸው ለምን እኔን ብቻ
ይነዝረኛል?
ለዚህ ሁኔታ መፈጠር የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፤
ምክንያቱም አንዳንዶች ስሜታቸው ለንዝረት በጣም የቀረበ
ሊሆን ይችላል፤ ሌላ ምክንያት የሚሆነው አንዳንዶቻችን
የእስታቲካ ኤሌትሪክ ሙሌት ከሌሎች በተለየ ሁኔታ በተለያየ
ምክንያት ልናከማች እንችላለን፤ ለዚህ ሁኔታ መለያየት
የምንጫመው ጫማ ሶል፣ የምንለብሰው ልብስ፣
የምንቀመጥበት ወንበርና ሌሎችም አስተዋፅኦ ሊኖራቸው
ይችላል፤ በነዚህ መንገዶች ያከማቸነው ብዙ የእስታቲካ
ኤሌትሪክ ሙሌት ካለን፣ ኤሌክትሪክ አስተላላፊ የሆነ እቃ ስንነካ
በአንድ ጊዜ ሙሊቱን ስለሚያጣ ከፍተኛ ንዝረት ሊሰማን
ይችላል፡፡
የአየር ሁኔታ ለእስታቲካ ኤሌትሪክ መፈጠር የሚያበረክተው
አስተዋፅኦ አለ ወይ?
የእስታቲካ ኤሌትሪክ በደረቅ አየር ሁኔታ ጊዜ የሚባባስና በስፋት
የሚታይ ሁኔታ ነው፤ እንደአጠቃላይ በቀዝቃዛ፣ በነፋሻማና
በደረቅ የአየር ሁኔታ ወቅት የእስታቲካ ኤሌትሪክ ንዝረት ሁኔታ
ብዙዎችን የሚያጋጥም ነው፤ በቤት ውስጥ ደግሞ ማሞቂያዎች
ወይም ቬንትሌተሮች ሁኔታውን ሊያባብሱ ይችላሉ፤ በተቃራኒው
ደግሞ ሞቃትና ርጥበታማ ሁኔታዎች የእስታቲካ ኤሌትሪክ
ክስተቶችን የሚቀንሱ የአየር ጠባዮች ናቸው፡፡
የእስታቲካ ኤሌትሪክ ንዝረት ለጤና አሳሳቢ የሚሆንበት ሁኔታ
አለ ወይ?
አብዛኛውን ጊዜ ክውታና ምቾት ከመንሳት ውጪ የከፋ ሁኔታ
አያጋጥምም፤ ምናልባት እንደ ችግር ሊታይ የሚችለው ሁኔታው
ሲያጋጥመን በደመነፍስ የምንወራጨው ነገር ከሌሎች ነገሮች
ጋር ሊያጋጨንና ልንጎዳ እንችላለን፤ ከዚህ በተለየ ሁኔታ ግን
በነዳጅ ማደያዎች አካባቢ፣ ለምሳሌ ነዳጅ ስንቀዳ ከብረት ጋር
በሚኖር ንክኪ ሁኔታው ቢፈጠር እሳት የመፈጠር አጋጣሚ
ሊከሰት ይችላል፡፡
የእስታቲካ ኤሌትሪክ ገጠመኝን መከላከል ይቻላል?
ይህንን ገጠመኝ ለማስቀረት ምናልባት ብዙ ሙከራዎችን
በማድረግ አብዛኞቹን ማስቀረት ወይም በሌላ ዘዴ በቁጥጥር
ስር ማዋል ይቻላል፤ ለምሳሌ በሮችን ስንከፍት ቀድመን በሩን
በቁልፍ መንካት፣ በበሮች ላይ የሚያጋጥመንን ንዝረት ሊያስቀር
ይችላል፡፡
ከመኪና ስንወርድ የሚያጋጥመንን ንዝረትስ እንዴት መከላከል
እንችላለን?
በመኪና ውስጥ በሚኖረን ቆይታ በወንበሩና በልብሳችን መካከል
የሚኖር መተሻሸትና ፍትጊያ የእስታቲካ ኤሌትሪክ ሁኔታ
እንዲከማች ያደርጋል፤ በዚህም ምክንየት የእስታቲካ ኤሌትሪክ
በሰውነታችን ላይ ይሰርፃል፤ በዚህ ሁኔታ ከመኪናው ለመውጣት
ስንሞክር በመተሻሸት የተፈጠረው ያልተመጣጠነ የቻርጅ
ክምችት አብሮን ይነሳል፤ በመሆኑም የሰውነታችን ቮልቴጅ
ከፍተኛ ይሆናል፤ በዚህ ሁኔታ በሩን ስንከፍት ከፍተኛ ንዝረት
ይሰማናል፤ ምክንያቱም የተከማቸውን ቻርጅ በአንድ ጊዜ
ስለምናጣ ነው፡፡ ይህንን ሁኔታ ለማስቀረት ከመኪናው
ከመውጣታችን በፊትና መሬቱን ከመርገጣችን በፊት
የመኪናውን በር ማዕቀፍ ብረት ብንነካ ንዝረቱ አያጋጥመንም፡፡

Pages: 1