ሄሎ ሀበሻ ምርጥ የሀበሻ መዝናኛ ሰፈር፣
ይህ ዌብ ሳይት ሀበሻን ከመላው አለም በማገናኘት የሚያወያይ
የሚያዝናና ዌብ ሳይት ወይም መድረክ ነው፥፥
ተሳተፉ ፣ ኮመንት አድርጉ ፣ የራሳችሁን ፃፉ
0 users browsing Politics - ፖለቲካ. | 1 guest
Pages: 1
Posted on 10-31-17, 05:03 pm


Karma: 90
Posts: 606/879
Since: 02-29-16

Last post: 37 days
Last view: 37 days
ምግብና ፖለቲካ

ዲ/ን ዳንኤል ክብረት

በየዓይነቱ የሚባል ምግብ መቼም ታውቃላችሁ፡፡ በጾም
ጊዜ የሚዘወተር የሀገራችን ምግብ ነው፡፡ አንዳንድ ቦታ
ሦስት ዓይነት ሲኖረው አንዳንድ ቦታ ደግሞ ሠላሳ
ዓይነት አለው፡፡ ‹በየዓይነቱ› የሚለውን የምግብ ቤቶች
መዝገበ ቃላት ሲተረጉመው ‹‹አንድ ቀይ የምሥር ወይም
የሽሮ ወጥ በእንጀራው መካከል ጎላ ብሎ ይቀመጥና እነ
አልጫ ሽሮ፣ እነ አልጫ ምስር፣ እነ ምጣድ ሽሮ፣ እነ
ቃሪያ፣ እነ ስልጆ፣ እነ ቲማቲም ፍትፍት፣ እነ አበሻ ጎመን፣
እነ የፈረንጅ ጎመን፣ እነ ሩዝ፣ እነ ሱፍ ፍትፍት፣ እነ ቀይ
ሥር፣ እነ ድንች ወጥ፣ እነ ተልባ ፍትፍት በዙሪያው
አጅበው ይሰለፋሉ›› ማለት ነው ይላል፡፡
በያይነቱ ሕግም አለው፡፡ ባይጻፍም እኛ ‹የበያይነቱ ሕግ›
ብለነዋል፡፡ በበያይነቱ ሕግ መሠረት በመካከል
የሚቀመጠው ዋናው ወጥ በቀላሉ የሚገኝና የሚሠራ
መሆን አለበት፡፡ ለዚህም ነው ወይ ምስር ወይም ሽሮ
የሚሆነው፡፡ ርካሽነቱ የጥሬ ዕቃው ብቻ ሳይሆን በአንድ
ትልቅ ድስት ውስጥ በቀላሉ በብዛት ሊሠራ የሚችል
ማለትም ነው፡፡ ለዚህም ሳይሆን አይቀርም ምሥርና ሽሮ
ወጥ፣ በልቅሶ ቤትም ዕድሮች በብዛት ይዘዋቸው
የሚመጡት፡፡ አንድ ድንኳን ሙሉ ለቀስተኛና ዕድርተኛ
ለማብላት እንደ ቀይ ምስርና ሽሮ ወጥ የሚበቃ
አይገኝም፡፡
ሁለተኛው የበያይነቱ የሕግ ዐንቀጽ ደግሞ በወጥ
ጭማሪ ጥያቄ ጊዜ ሊጨመር የሚችለው ዋናው ወጥ
(ቀይ ሽሮው ወይም ምሥር ወጡ) ነው ይላል፡፡ እንጀራ
ሲተርፍ ወይም እንጀራ ሲጨመር የወጥ ጭማሪ
ቢጠየቅ ዋናውን ወጥ ማስጨመር ይቻላል፡፡
ሦስተኛው የበያይነቱ ሕግ በዋናው ወጥ ዙሪያ
ለሚመጡት ዓይነቶች የቁጥር መጠን እንደሌላቸው
ይደነግጋል፡፡ ሦስትም ሆኑ አሥራ ሦስት ችግር
የለውም፡፡ ቁም ነገሩ ዋናውን ወጥ አጅበው በዙሪያው
መኮልኮላቸው ነው፡፡ አራተኛውና እነዚህን በዙሪያው ያሉ
ወጦችን የሚመለከተው ሕግ ደግሞ እነዚህ ወጦች
ካለቁ አለቁ ነው ይላል፡፡ ዓይነት አይጨመርም፡፡ ዓይነት
አለመጨመሩ ብቻ ሳይሆን በበያይነቱ ሕግ ዐንቀጽ አራት
ንዑስ ዐንቀጽ አንድ መሠረት በምግብ ቤቱ ውስጥ
ዋናው ወጥ አያልቅም እንጂ ዓይነት ሆነው የሚቀርቡት
ወጦች ግን ሊያልቁ እንደሚችሉ ይደነግጋል፡፡
እንዲያውም በንዑስ ንዑስ ዐንቀጹ ላይ የዓይነቶቹ
መጠን የምግቡ ሰዓት ሲጀመርና ሲያልቅ ሊለያይ
እንደሚችልም ያስቀምጣል፡፡ ዋናው ወጥ ግን በብዛት
ስለሚሠራ አያልቅም፡፡
አምስተኛው የበያይነቱ ሕግ ዐንቀጽ ዋናውን ወጥ
አጅበው የሚቀርቡት ዓይነት ወጦች ‹ወጥ› ወይም
‹ዓይነት› የሚለውን ስም እስከያዙ ድረስ የፈለጉትን
ዓይነት፣ መጠን፣ ቅርጽና ጣዕም ሊኖራቸው እንደሚችል
ይደነግጋል፡፡ ለምሳሌ ክክ ወጥ፣ ምጣድ ሽሮ፣ አልጫ
ሽሮና አተር ፍትፍት በቅርጽና በስም ካልሆነ በቀር አንድ
ዓይነት ናቸው፡፡ ዞሮ ዞሮ ያው ሽሮ ነው፡፡ ነገር ግን
በየራሳቸው ስምና ቅርጽ ይዘው ‹ዓይነት› ሆነው መቅረብ
እንደሚችሉ ‹የበያይነቱ ሕግ ይፈቅድላቸዋል፡፡
በበያይነቱ ሕግ ዐንቀጽ ስድስት መሠረት አንድ ምግብ
‹ዓይነት› ሆኖ የሚቀርበው በዋናነት ለመልኩና ቅርጹ
እንጂ በውስጡ ላለው ይዘት እንዳልሆነ ይደነግጋል፡፡
ለዚህም ሳይሆን አይቀርም እነ አበሻ ጎመን፣ እነ ጥቅል
ጎመንና እነ ኪያር እሳት ካደበናቸው የምግብ ይዘታቸው
በሙሉ እንደሚጠፋ ቢታወቅም ቅሉ፣ ድብን ብለው
በስለው ‹ዓይነት› ሆነው ለመቅረብ የቻሉት፡፡
በበያይነቱ ሕግ ዐንቀጽ ስድስት ንዑስ ዐንቀጽ ሦስት
መሠረት ሁለት የበያይነቱ ወጦች የይዘትም ሆነ የቅርጽ
ልዩነት ባይኖራቸውም ስማቸው ከተለያየ እንደ አንድ
ወጥ ተመዝግበው መንቀሳቀስ ይችላሉ ይላል፡፡ አልጫ
ምስርና ቀይ ምስር፣ አልጫ ድንችና ቀይ ድንች
ቅርጻቸውም ሆነ ይዘታቸው አንድ ቢሆንም የስም ልዩነት
ስላላቸው ግን ይኼው በዓይነትነት ተመዝግበው
ቀጥለዋል፡፡
በበያይነቱ ውስጥ እንደ ቃሪያ የሚያቃጥሉ፣ እንደ ምስር
የሚጎረብጡ፣ እንደ ተልባ ፍትፍት የሚለሰልሱ፣ እንደ
ሩዝ የአበሻ ምግብ ውስጥ ለምን እንደመጡ
የማይታወቁ፣ እንደ ቲማቲም ፍትፍት የንጽሕናቸው ጉዳይ
ሆድ ሲያጮኽ የሚውል፣ እንደ ስልጆና እንደ አተር
ፍትፍት በአንድ ጉርሻ የሚያልቁ ምግቦችም እንዲካተቱ
ሕጉ ይፈቅድላቸዋል፡፡
በበያይነቱ ሕግ ዐንቀጽ ዐሥር መሠረት ዛሬ አንድ ዓይነት
ሆኖ የቀረበ ወጥ ነገ ተለያይቶ ሁለት፣ ሁለት ሆኖ
የነበረም እንድ ሆኖ ለመቅረብ እንደሚችል ይፈቅዳል፡፡
ለየብቻቸው ሲቀርቡ የነበሩት ቀሪያ፣ ቲማቲምና እንጀራ
ከቅርብ ዘመናት ወዲህ የቲማቲም ፍትፍት ተብለው
ኅብረት መሥርተው መጥተዋል፡፡ ‹ሽሮ ወጥ› ተብለው
አንድ ላይ የነበሩት ‹ሽሮ ፈሰስ›ና ‹ሽሮ ተጋቢኖ› ሆነው
በየራሳቸው መጥተዋል፡፡
ይህን የበያይነቱን ሕግ አይተን እስኪ የሀገራችን
የፖለቲካ ሕግና ባህል እንገምግመው፡፡ ፖለቲካችን
ከበያይነቷችን ወይም በያይነቷችን ከፖለቲካችን ተወስዶ
ሊሆን ከቻለስ?
በበያይነቱ ሕግ አንድ ዋና ወጥ እንዳለው ሁሉ
በሀገራችንም አንድ አውራ ፓርቲ አለ፡፡ ሌሎቹ
በመጠናቸው አነስ አነስ ያሉ ወጦች ዋናውን ወጥ
አጅበው እንደሚቀመጡ ሁሉ በሀገራችን ያሉት
ከብሔረሰቦች ቁጥር የበለጡት ፓርቲዎችም ይህን
አውራ ፓርቲ አጅበው የሚኖሩ ናቸው፡፡ ይህ በበያይነቱ
የሚገኝ ዋናው ወጥ ይኼው በያይነቱ ከተፈጠረ ጀምሮ
ምስር ዋና ሆኖ የመካከሉን ዋና ቦታ እንደያዘው አለ፤
አንድም ዓይነት ሆኖ የገባ ወጥ ቦታውን እንዳልወሰደው
ሁሉ በሀገራችንም ይኼው ዋናውም ወጥ ሆነ ዓይነቶቹ
ዛሬም በዚያው ቦታቸው ናቸው፡፡
በበያይነቱ ሕግ ዋናው ወጥ ይጨመራል እንጂ ዓይነት
አይጨመርም፡፡ በሀገራችን ፖለቲካም አውራው
እየጨመረም እየተጨመረም ይኼዳል እንጂ ዓይነቶቹ
ካለቁ አለቁ ነው፡፡ ስንት ፓርቲ ዓይነት ሆኖ በሆነ
የምርጫ ዘመን ከመጣ በኋላ በሌላ ጊዜ ‹ጨምሩ›
ስንል ‹አልቋል፤ ከፈለጋችሁ ምስር ጨምሩ› ተብለናል፡፡
በበያይነቱ ወጥ ዋናው ወጥ በትልቁ ሰታቴ ነው
የሚሠራው፤ እንዳያልቅ፡፡ በሀገራችንም ዋናው ፓርቲ
በትልቁ ነው የተሠራው፡፡ ወደ ዋናው ወጥ ሰታቴ
የማይገባ እህል፣ የማይጨመር ውኃ፣ የማይደረግ
ቅመም የለም፡፡ ችግሩ አንዳንዱ በሚገባ ያልተቀመመ፣
አንዳንዱ ‹ኤክስፓየር› ያደረገ፣ አንዳንዱ ምን ሳይጠቅም
እንዲሁ የገባ፣ አንዳንዱ እንደ ሽንኩርቱ ያረረ፣ እየሆነ
ነው ችግሩ፡፡ ወጥ ሠሪዎቹም ዋናው ዓላማቸው ወጡ
እንዲሰፋ፣ እንዲበዛ፤ ከዚያም አልፎ ሌሎቹ ዓይነቶች
ሲያልቁ ዋናው ወጥ እንዳያልቅ ማድረግ ነውና ያገኙትን
የእህል ዓይነት ሁሉ እያስገቡበት ተቸገርን፡፡
በልቅሶ ቤትም፣ በግብዣም፣ በድግስም፣ በቤታችንም፣
በየመሥሪያ ቤቱ ካፍቴሪያዎችም፣ በብዛትና በስፋት
የምናገኘው ይኼንኑ ዋናውን ወጥ ሆነ፡፡ አንዳንዶች
ለዚህ የሚሰጡት ምክንያት ይህንን ዋናውን ወጥ
መሥራት ቀላል፣ ብዙም ችሎታ የማይጠይቅ፣ ርካሽና
በትልቅ ዕቃ የሚሠራ፣ ብዙም መሥዋዕትነት
የማይጠይቅ ስለሆነ ነው ብለዋል፡፡
እንደ በያይነቱ ሁሉ የሀገራችን ፓርቲዎች የቁጥር መጠን
የላቸውም፤ በብሔረሰቦች ቁጥር መጠን መስሎን ነበር፤
አሁንማ ከዚያም ቁጥር አለፈ፡፡ አንዳንዶቹ የበያይነቱ
ወጦች በማንኪያ ተመጥነው የሚቀርቡት ከአንድ ጉራሽ
እንደማያልፉ ሁሉ፣ አንዳንዶቹ ፓርቲዎች በዐሥር ሰው
ይመሠረቱና ከአንድ ምርጫ ወይም ከአንድ ስብሰባ፣
አለፍ ካለም ከአንድ ሰላማዊ ሰልፍ አያልፉም፡፡ ቀይ
ሽሮ፣ አልጫ ሽሮ፣ ሽሮ ፍትፍት፣ ክክ ወጥ፣ አተር ፍትፍት
እየተባለ አንዱን ባቄላ ወይም አተር በዐሥር ዓይነት
እንደሚያመጡት ሁሉ ከስማቸው በቀር የፕሮግራም፣
የግብ፣ የአደረጃጀትና የአካሄድ ልዩነት የሌላቸው
ፓርቲዎች ሞልተውናል፡፡ ልዩነታቸው አንዱ አበበን ነጻ
ሲያወጣ ሌላኛው ጫልቱን፣ ሌላኛው ደግሞ ኪሮስን
የቀረውም ደንቦባን ነጻ ማውጣቱ ነው፡፡
በበያይነቱ ውስጥ እንደሆነው ሁሉ እንደ ቃሪያ
አሠራራቸው የሚያቃጥል፣ እንደ ስልጆ የሚሰነፍጥ፣
እንደ ቀይ ሥር መልክ እንጂ ይዘት የሌላቸው፣ እንደ
ሩዝ እንዴት ፓርቲ ሊሆኑ እንደቻሉ ግራ የሚያጋቡ፣ እንደ
ቲማቲም ፍትፍት ሆድ ማስጮህ እንጂ አእምሮ መገንባት
የማይችሉ ፓርቲዎችም አሉን፡፡
በበያይነቱ ወጥ ውስጥ እንዳሉት የሐበሻ ጎመንና ጥቅል
ጎመን፤ በፖለቲካው እሳት በመንተክተካቸው የተነሣ
የምግብ ይዘታቸው የጠፋ፡፡ ቢበሏቸው የማይጠቅሙ፣
ቢተዋቸው የማይጎዱ ዓይነት ፓርቲዎችም አሉን፡፡ እንደ
ቃሪያና ቲማቲም ለየብቻ ጀምረው እንደ ‹ቲማቲም
ፍትፍት› አንድ ሆነው የመጡ፣ እንደ ‹ሽሮ ወጥ› እንደ
ሆነው ጀምረው እንደ ሽሮ ፈስስና ሽሮ ተጋቢኖ
ተለያይተው የቀጠሉ ፓርቲዎችም አሉን፡፡
በበያይነቱ ምግብ የምግብ ሰዓት ሲጀመር የነበሩት
ዓይነቶች እያለቁ ሄደው በስተ መጨረሻ በያይነቱ ራሱ
አልቆ ‹ምስር ወይም ሽሮ ነው ያለን› እንደሚባለው ሁሉ
በሀገራችን ከሃያ ዓመት በፊት ምርጫና ዘመቻ ሲጀመር
እንደ አሸን ፈልተው የነበሩት ‹በዴሕ› ና በ‹ዴድ› የሚጠሩ
ፓርቲዎች አሁን የት እንደደረሱ የሚያውቅ የለም፡፡
ሁሉም ዓይነቶች አልቀው ዋናው ወጥ ብቻ ቀረ፡፡
እንግዲህ የኛ የፖለቲካ ሥርዓት በያይነቱ ምግባችንን
ሳይመስል አይቀርም፡፡ ምናልባት ምግቡ ከፖለቲካው
ይቀድማልና ፖለቲካው ከምግቡ አሠራሩን ቀድቶት
እንደሆነ እስኪ እንመርምረው፡፡ ምናልባት በያይነቱን
ብናስተካክለው ፖለቲካው ይስተካከል ይሆን?
ቸር ይግጠመን፡፡
Pages: 1