ሄሎ ሀበሻ ምርጥ የሀበሻ መዝናኛ ሰፈር፣
ይህ ዌብ ሳይት ሀበሻን ከመላው አለም በማገናኘት የሚያወያይ
የሚያዝናና ዌብ ሳይት ወይም መድረክ ነው፥፥
ተሳተፉ ፣ ኮመንት አድርጉ ፣ የራሳችሁን ፃፉ
0 users browsing ልጅነት. | 1 guest
Pages: 1
Posted on 10-14-17, 11:38 pm


Karma: 90
Posts: 582/887
Since: 02-29-16

Last post: 373 days
Last view: 373 days
¶ ስለ ፍቅር ለዋሸሁሽ

(አክረም ሀበሻዊ)

ልጅነት ከእውነት ጋር ያልተኳረፈ ማንነት ነው። የልጅነት መውደቅ የጉብዝና ወር መቆም ነው! የልጅነት ማጣት የዛሬ የማንነት ሙላት ነው። በልጅነቱ በጠንካራ ስብዕና ያልተቀረፀ ትውልድ አሻራው ያረፈበትን ዘመን ተሻጋሪ ስራ ቀርፆ ማኖር አይቻለውም።
ዛሬ የቆምነበት የተነሳንበትንና ያሳለፍነውን ያሳብቃል።
አዎ! ልጅ ሆኖ ያላደገ አዋቂ አይሆንም!!!
ዛሬም እንደትላንቱ የትዝታ ዥዋ ዥዌ ከወዲህና ከወዲያ ያላጋኛል፣ ደጉን ዘመን ያስናፍቀኛል፣ የልጅነቴ የውበት ፈርጥ የሆነችው ማማርን አይኔ ላይ እያዋለ ሆድ ያስብሰኛል፤ እብዷን የፍቅር ሴት በማየው ሁሉ እየሳለ ምናለ የጊዜን ታንኳ የኃሊት ቀዝፌ ዳግም በዘመኗ ብገኝ ያስብለኛል።
በጊዜ ውስጥ ሁሉም አለ, ህይወትም ፣ ውበትም ፣ ሞትም፣ አልፈን እንኳን የማያልፍ ትዝታም!"
"ትዝታ አያረጅም
ፍቅር አያረጅም
ውበት ቢጠወልግ
ሰውነት ቢጃጅም!"
አይደል ያለው ጋሼ ሚኒሊክ?
ልጅነት የገነባውን እምነት፣ አዋቂነት በሚወልደው ጥርጣሬ ያፈርሰዋል! እምነትም ይቀበራል! አንድ መሆን ያስጠይቃል። ሁሉም እያለ ሁሉም ይታጣል።
ዛሬ ያን ዘመን ሳስብ ነገሩ ሁሉ ይናፍቀኛል።
ልጅነትን ይለኛል,,,,,,!
የማልናፍቀው የለም,,,,,,, ማማር፣ እብዷ፣ ሰፈሩ፣ አየሩ፣ የጎረቤት ልጆች፣ የላይ ሰፈር ልጆች፣ ናና ከረሜላ በነፃ የሚሰጠኝ ባለ ሱቁ ሙስጤ፣ የጎረቤት እናቶች፣ ቤታቸው ተደብቀን እየገባን ፕሪም የምንሰርቃቸው የማርሸት እናት፣ እነ ስምረት ቤት ለጥየቃ ሲመጣ አቡወለድ ገዝቶ የሚያካፍለን የስምረት አጎት፣ ባገኘኝ ቁጥር የሚኮረኩመኝ ሀርደኛው ሳሚ፣ ኪዳነ ምህረት ጀርባ ያለው የምንዋኝበት ወንዝ፣ የያኔው የልጅነት ቀኔ, ቀኑ፣ ምሽቱ፣ ዝናቡ፣ ደመናው,,,,,,,,,,,, ሁሉም ይናፍቀኛል!!!
ልጅነት ታዛዥነትን ይለግስሀል ኃላፊነትን ይመርቅልሀል። በልጅነት ብትዋሽ እንኳን አትዋሽም! ዶሮዋ የጣለችውን እንቁላል ብትሰብርና እናትህ ተቆጥተው, ማነው የሰበረው? ቢሉህ ልትል የምትችለው "የሰበርኩትን እንቁላል እኔ አልሰበርኩም!" ነው። የልጅነት ውሸት ውስጥ እውነቱ አለ!! ልጅነት እንዲያ ነበር,,,,,,,,,,,,,!!
በልጅነት ውሸቴ ውስጥ ያለውን እውነት ማማር አልተረዳችኝም! ብትረዳኝማ ከእውነቱ የመሸሽ አቅሙ ባልኖራት ነበር።
የልጅነት ውሸት ውስጥ ያለውን እውነት የተረዳችው እብዷ ሴት መሆኗ አሰብሁ። በሀሳቤም ወደ እብዷ የፍቅር ሴት ሄድኩኝ፤ በጉብዝና ዘመኗ ከነ ልጅነት እውነቷ የተገኘች የስብዕና መምህር ሆና ታየችኝ። ስብዕናን ሳስብ ከቀኖች በአንዱ እብዷ ዘንድ የገጠመኝ ታወሰኝ፦
እብዷን ተከትዬ ቸርችልን ወረድሁ ወደ ካቴድራል ት/ቤት መንገድ ስትታጠፍ ተከተልኳት። ከቶሞካ የወጡ እናትና ልጅ ከፊታችን መጡ፤ አፍ ያልፈታችው ጥንጥዬዋ ሚሚ እብዷ ሴት ጋር ስትደርስ ፍልቅልቅ ብላ እጇን ዘረጋች እናቷ በፍጥነት የልጇን እጅ ሰበሰበች ዞራ እንዳታያትም ከለከለች፤ መጠየፏም ከፊቷ ተነበበ፤ እብዷ ሴትም ለህፃኗ ለሰላምታ የሰነዘረችውን እጅ ሳትመልስ ፈዛ ቀረች፣ ፊቷ ተለዋወጠ፣ እንባዋ ጉንጯን ለማራስ ጊዜ አልወሰደበትም። በቁጣ ጮኸች፦
" ያንቺን መውለድ ከማስወረድ ለይቼ አላየውም!!!
ላንቺ አላዝንም የምታመልኪው ጨርቅ ከእውነት ጋር አቆራርጦሻል የማዝነውስ ለሷ ነፍሷ ለሚያምረው ትንሽዬ ጨረቃ, በብርሀን የልቧን ብርሀን ለመቀማት ለምትታገያት! ለሷ ነው የማዝነው!!
ልጅን መውለድ እና ልጅን መስራት ይለያያል! ወለድሻት እንጂ አልሰራሻትም! ሰሪዋ ምድርን የሰራው ነው። የዶሮዋ ጫጩት የእንቁላሉ ቅርፊት ማህፀን ውስጥ የነበረ መሆኑን እወቂ!
ቅርፊት ነሽ አልልሽም ምክንያቱም ሰው የሆነውን መንገር ምንም የመንገር ያህል ነውና።
ያደገ ሁሉ የተወለደ ከመሰለሽ ተሳስተሻል! እንዴት እንዳትይኝ መልሱ አንቺው ዘንድ አለና,,, እየገደሉ ማሳደግ!"
ሴትዬዋ ሚጣን ይዛ ርቃ ሄዳለች እብዷ መናገሯን ቀጥላለች,,,,,,,, ቶሞካ ደጃፍ ቆማ ለአላፊ አግዳሚው እንዲሰማ አድርጋ ጠንካራ መልዕክቷን በግጥም ተወጣች፦
"መለኪያቹ በዝቶ ጠፋና ልካችሁ
ራስን መሆን ሞቶ በዛና መንጋችሁ
ሳሩ ተረጋግጦ አፈር ሆነ ህልማችሁ
በመለኪያ ብዛት ልክነት ራቃቹ፤
ጨርቅ ነፍስን ተካ
ብር እውነትን ለካ
እርጥቡ ደረቀ ማፍቀር ጠወለገ
መስጠትም አለቀ፤
ሰው "ሰው!" ለማለት መለኪያ አበጁለት
በልካቸው ሰፍተው በመልካቸው ቀቡት
ሀገሩ ሁሉ አንድ አይነት
ይሄ ነው እንግዲህ ሬዲሜድ ማንነት!!!
የህፃኗም ተስፋ,,,,,
ባሰናዳቹላት የክፋት መለኪያ
ሳይመሽ አንቀላፋ!
ዳዴ ከማቆሟ፣ ደርሳ ከመቆሟ
መቼ አላቿትና ወፏ ቆመችልን
ክፋት ቀባብታቹ ነጠቃቿት እንጂ
ያልተኖረ ዕድሜዋን!!!
አዬ ሰው መሆን,,,,,,,, አዬ እናትነት
በባዶ መሶብ አብልቶን ነበር
ሳይቀይረው ወረት!!
በነሱ መለኪያ ልኬን ባያገኙ
ጨርቄን ቀሙኝና ጨርቋን ጣለች አሉኝ!
ደግሞ እኮ የሚገርመው
በጨርቄ አጊጠው ሸሹኝ ተጠይፈው!!
እኔስ መች ሞኝ ሆንኩኝ
እውነትን በጨርቅ የምለውጥ
ነፍሴን አስርቤ ለሆዴ የማምጥ!
ኤዲያ! እንዲህ ካለው ኑረት
እብደቴን ወደድኩት!!
እብድም ብሆን ብትሰሙኝ ምናል?
ማስተዋልን ለተሰጠ,,,,,,,
የመኖር መድሀኒት ከሙት ላይ ይገኛል!!
በሀሰት መለኪያቹ በምትመዝኑበት
እውነቷን አትቀሟት!
ለከሰረ መሻት ትውልድ አይሰዋ
ለሀገሯ ትኑር እንቦቃቅላዋ!!!"
ብዙ ትምህርት ካገኘሁበት የዕብዷ ትውስታ ተመለስሁ። እውነትም የስብዕና መምህር!! እብዷን ለማናገር የያዝኩት ቀጠሮ ታወሰኝና ከቤታችን ወጥቼ ወዳለችበት ሄድሁ,,,,,,,, ህይወት ራሷ መሄድ አይደለች? አንድም ጊዜ እየሄድን እንሄዳለን ሌላም ጊዜ በትዝታ!!!!
"ትዝታ አያረጅም
ፍቅር አያረጅም
ውበት ቢጠወልግ
ሰውነት ቢጃጅም!"
ጋሼ ሚኒሊክ ያ የአባት ጠረን ያለን ሽበታሙ ሰውዬን ዜማ እያንጎራጎርኩ ወጣሁ። ያ እንደውም ልክ እንደኔ "ስለ ፍቅር የዋሸው!" ሰውዬ እንደውም፦
"ጥያቄው ቢስጨንቀኝ ስለ ፍቅራችን ትዝታ
አልወዳትም አልኳቸው እንዲያገኙ ደስታ
እኔስ ውሸቴን ነው ይቅርታ አርጊልኝ!"
ፍቅር እስካለ ስለ ፍቅር የሚዋሽ ውሸትም ይኖራል።
ፍቅር፣ ውሸት፣ ናፍቆትና ትዝታ ሁሉም ይኖራሉ! ይቀጥላል,,,,,,,,,,,,,,,

Pages: 1