ሄሎ ሀበሻ ምርጥ የሀበሻ መዝናኛ ሰፈር፣
ይህ ዌብ ሳይት ሀበሻን ከመላው አለም በማገናኘት የሚያወያይ
የሚያዝናና ዌብ ሳይት ወይም መድረክ ነው፥፥
ተሳተፉ ፣ ኮመንት አድርጉ ፣ የራሳችሁን ፃፉ
0 users browsing Football / Soccer. | 1 guest | 1 bot
Pages: 1
Posted on 09-05-17, 05:44 am


Karma: 100
Posts: 299/756
Since: 03-20-17

Last post: 15 hours
Last view: 15 hours
⚽ የባርሴሎናው ኮከብ የሊዮኔል አንድሬስ ሜሲ የእግር-ኴስ የህይዎት ታሪክ፣ የዝውውር ሁኔታዎቹ፣ የግል ህይዎቱ እንዲሁም ሌሎች ተጨዋቹን የተመለከቱ ዳሰሳዎች! - ክፍል አንድ
ቶሎ-ቶሎ ዜናዎችን እንድናደርሳችሁና ምንም ዜና እንዳያመልጣቹ ከታች Like ማረጉን አትርሱ!
★★★★★★★★★★★★★★★★★★★★★
▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔
✔ ከአንድ መንደር በተለያዩ ዘርፎች በዓለም ላይ ዝናን ያተረፉ ክብርና ሞገስን የተጎናፀፉ ጀግኖችን ማፍራት እንዴት ዕድለኛነት ነው። በታሪክ መዛግብት ስማቸውን በደማቅ ቀለም ስፃፉ ተምሳሌቶችን አፍርታለች። ከአርጀንቲና ርዕሰ መዲና ቦነስ አይረስ 300 ኪሎ ሜትሮችን ርቃ የምትገኘው ሮዛሪዮ!
▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔
✔ አዎ ይቺ ከተማ ቼጎቬራን እና ሊዮኔል ሜሲን ለዓለም አበርክታለች! ሜሲ በእግር ኳስ ዘርፍ ቼን ደግሞ በነፃነት ትግል መሪነት ዘርፍ!! ስለ ሮዛሪዮ ይህን ማንሳቴ ወደ ዋናው ፅሁፌ መንደርደሪያ ይሁነኝ ብዬ እንጂ ስለትንሿ ከተማ ብዙ የምነግራቹ ነገር ኖሮኝ አይደለም ሆኖም ግን ከዚህች ትንሽ መንደር ስለወጣው ሊዮኔል ሜሲ ልነግራችሁ እንጂ...
▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔
✔ 169 ሳንቲ ሜትር ቁመት አለው::በ1987 እንደ ጎርጎሮሳውያን መቁጠሪያ ዘመን በወርሃ ጥር 24 ቀን በራዕይ ትነግሳለህ በትንቢት ተዓምርን ትሰራለህ ያልተባለለት ጨቅላ በአርጀንቲና ሮዛሪዮ ከተማ ይችን ዓለም ተቀላቀለ። አባቱ ጆርጌ ሆራሲዮ ሜሲ በአንድ የብረታ ብረት ፋብሪካ ውስጥ ቅጥረኛ የነበረ ሲሆን እናቱ ደግሞ ሲሊያ ማሪያ ኩኩቲን የግማሽ ሰዓት የፅዳት ሰራተኛ ነበረች። የቤተሰቡ ብዛት በሁለት ወንድሞቹ ማለትም ሮዲሪጎ እና ማትያስ እንዲሁም አንድ እህቱ ማሪያ ሶል ጋር ስድስት ሆነዋል...ወደ እግር ኳስ ህይወቱ አመራን...
▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔
✔ ሜሲ እግር ኳስን አንድ ብሎ የጀመረው ገና በአምስት ዓመቱ በአባቱ በሚሰለጥነው ቡድን ውስጥ ነበር ጊዜው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 1995 ነበር! በልጅነት ቡድኑ የልብ ምት የነበረው ሜሲ ይጫወትለት የነበረው ቡድን የ"87 ማሽን" የሚል ተቀፅላን ተጎናፅፈዋል ይህም የሆነው በአራት አመታት ውስጥ የሜሲ ቡድን ሽንፈትን የቀመሰው በአንድ ጨዋታ ብቻ ስለነበረ ነው። በዚህ ጊዜ ነበር የወቅቱ ኮከብ ተጫዋች ዕድገቱ ከዕድሜው ጋር አለመጣጣም የተስተዋለበት በሀኪም ሲመረመር የዕድገት ሆርሞን እጥረት እንደገጠመው ተረጋግጧል። ዕድሜው ገና አስራ አንድ ብቻ ነበር። በዚህ ጊዜ ዕድገቱን በህክምና ለማስቀጠል ደግሞ ከፍተኛ ወጪ አስፈልጏል::
▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔
✔ የሜሲ ቤተሰብ የአቅም ውስንነት ልጃቸው የገጠመውን ችግር ለመቅረፍ አላስቻላቸውም ነበር:: በዚህ ጭንቅ ውስጥ በነበሩበት ወቅት ታዲያ ከወደ ስፔን የጭንቅ ደራሽ ድምፅን የሰሙት የሜሲ ቤተሰቦች የያኔው የካታላኑ ቡድን ባርሴሎና አሰልጣኝ የነበረው ካርለስ ረክሳች ሜሲ በሚደረግለት የህክምና እና ወጪው ምትክ የባርሴሎና ወጣቶች ማሰልጠኛ ወደሆነው ላሜሲያ የሚቀላቀልበት ስምምነት ሀሳብ የቀረበላቸው ምንም ማቅማማት ያላሳዩት የጆርጌ ሆራሲዮ ቤተሰብ ከሜሲ ጋር በመሆን አባቱ እስከነ ጏዛቸው ወደ ስፔን ጉዞ አደረጉ።
▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔
✔ ባርሴሎናም በቃላቸው መሰረት የብረታ ብረት ፋብሪከ ተቀጣሪው ጆርጌ ሆራሲዮ መክፈል ያልቻሉትን የአሜሪካን ዶላር ክፍያ ፈፅመው የሜሲን ህክምና ያጠናቀቁት።መሰረቱን ሮዛሪዮ ያደረገው ኒዌልስ ኦለድ ቦይስ ለሜሲ ህከምና ወጪ ለማውጣት ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ህፃኑን ልጀ በህክምና ለመደገፍ የስፔኑ ባርሴሎና 45 ቀናትን የፈጀ 1500 አሜሪካ ዶላር ያስወጣ ህክምናን ፈፅመዋል።በላመሲያ ማዕከል ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መሰልጠን የጀመረው ሊዮኔል ሜሲ ከበፊቱ እጅግ የበለጠ ብቃቱን በማሳየት በማዕከሉ የሚገኙትን ሰዎች አብዝቶ አስገረመ። የዋና ቡድኑ አሰልጣኝ የነበረው ሆላንዳዊው ፍራንክ ራይካርድም በአርጀንቲናዊው የኯስ ችሎታ ተማርኯል እናም በዋናው ቡድን ውስጥ ሊያሰልፈው ፍላጎት አደረበት።
▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔
✔ በብሉግራናው 2ተኛ ቡድን አስራ አራት ጨዋታዎችን አድርጎ ሃያ አንድ ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ወደ ዋናው ቡድን ለማደግ የሚያደርገውን ሩጫ ተያያዘው። በፈረንጆች 2004 ዓመት ምህረት በስፔን ላ ሊጋ ባርሴሎና ከኢስፖኞል ጋር 34000 ደጋፊዎች በታደሙበት ባርሴሎና በዴኮ ግብ አንድ ለባዶ እየመራ የጨዋታው መገባደጃ ደረሰ... ስምንት ደቂቃዎች ቀርቶታል ባለፀጉር ወጣት መስመር ላይ ዘለል ዘለል እያለ ወጣ..የጨዋታው ግብ አስቆጣሪ ፖርቱጋላዊው ዴኮ ተቀይሮ ወጣ...17 ዓመት ከ3 ወር ከ22 ቀናትን ብቻ ዕድሜ ያለው አንድ አርጀንቲናዊ 30 ቁጥር መለያን ለብሶ የሜዳው ሳር ላይ መሯሯጥ ጀመረ። ይህ እንግዲህ የአሁኑ ጥበበኛ የያኔው ትዝታ ነበር ጨዋታው በአንድ ለባዶ ውጤት
ተጠናቀቀ::
▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔
✔ በ2005 እ.ኤ.አ የስፔን መንግስት ዜግነትን ሰጠው ከሰባት ወራት በሗላ በ34ኛው ሳምንት የስፓኒሽ ላሊጋ ሜሲ ባርሴሎና አልባሴቴን ሁለት ለባዶ ሲረታ ከሮናልኒሆ ያገኛትን አንድ ግብ አስቆጠረ።ይህም በባርሴሎና ዋናው ቡድን የመጀመሪያ ግቡ ሆና ተመዝግባለች። አስራ አንደኛ የውድድር ዘመኑን በካታላኑ ማሊያ እያሳለፈ የሚገኘው ምትሀተኛው ሜሲ በ2006 አርሰናልን አሸንፈው የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን አሸንፏል።
▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔
✔ ሜሲ በላ ሊጋው የመጀመሪያ ተሳትፎ የምንግዜም ወጣቱ ተሰላፊ ሲሰኝ ከጥቂት ወራት በሗላ አልባሴቴ ላይ ከመረብ ያሳረፋት ግብ ደግሞ በተመሳሳይ አዲስ ክብርን አጎናፅፋዋለች የምንገዜም ወጣቱ በትንሽ ዕድሜው ግብ ያስቆጠረ ተጫዋች በሚል። ከጥቂት ዓመት በሗላ በትንሽ ዕድሜ ግብ ያስቆጠረ የሚለውን ስያሜ በሌላኛው የላሜሲያ ምሩቅ ቦያን ኪሪኪች ተነጥቋል።በዚያው 2004 እ.ኤ.አ. ሜሲ ለሀገሩ አርጀንቲና የበኩሉን እንዲያበረክት ሀገረ አርጀንቲና ጥሪዋን አቀረበች ፊፋ በሚያዘጋጀው የወጣቶች አለም ዋንጫ ውድድር ተሳትፎን ማድረግ ጀመረ።
▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔
✔ የወጣቶቹ ዓለም ዋንጫም ተጀመረ....በጉዞ ሂደት የሜሲ ሀገር ለፍፃሜ ደረሰች አፍሪካዊት ሀገር ናይጄሪያ ደግሞ ሌላኛዋ የዋንጫ ተፋላሚ የፍፃሜ ጨዋታው በአርጀንቲና ሁለት ለአንድ አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ሜሲ ሁለቱንም ግቦች በፍፁም ቅጣት ምት ማስቆጠር ችሏል...የውድድሩን የወርቅ ጫማም የግሉ አደረገ....2005 ለሜሲ አዳዲስ ነገሮች ማሳየቷን እንደቀጠለች ነው! የወጣቶቹን የዓለም ዋንጫ ከ20 ዓመት በታች የአርጀንቲና ቡድን ጋር ካነሳ በሗላ ለዋናው ብሄራዊ ቡድን መጫወቻ ጊዜን ለማግኘት አንድ ወር ብቻ ጠብቇል።
▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔
✔ ሃገረ አርጀንቲና አዲሱ ንጉሷን ጥሪ አቅርባለታለች....ትንሹልጅም ጥሪውን
ተቀብሏል....በነገራች ላይ ሜሲ ያኔ ዜግነቱን ስፔናዊ እንዲሆን ፍቃድ የሰጡት ስፔናውያን ለስፔን ብሄራዊ ቡድን ተጫወትልን ባሉት ጊዜ እሱም "እኔ አርጀንቲናዊ ነኝ" ብሏቸው የአሻፈረኝ መልስ ጥያቄያቸውን ውድቅ
አድርጎባቸዋል። ሜሲ አሁን የመጀመሪያ ሀገራዊ ግዴታውን ሊወጣ በሀገሩ ቡድን ውስጥ ስሙ ተካቷል....ቀጠሮው ደረሰ
አርጀንቲና ሀንጋሪን ነው የምትገጥመው::
▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔
✔ በጨዋታው አጋማሽ ሜሲ ተቀይሮ ወደ ሜዳ ገባ ታሪክም ሌላ ስለሜሲ የሚወራ ነጥብ አሰፈረ....ሜሲ በጨዋታው ሜዳው ላይ የቆየው ለ47 ሰከንዶች ብቻ ነበር ኯስ ሲያንከባልል መለያውን ይዞ ለማስቀረት የሞከረውን የሀንጋሪ ተጫዋች ቪያሞስ ቫንሻክን ባልተገባ አጨዋወት በክርኑ ተማቶ ገና ምንም ሳይፈነጭ ወደ መልበሻ ክፍል ተባሯል....ይህ እንግዲ የመጀመሪያ የሜሲ ይፋዊ የሀገር ግጥሚያ ክስተት ነበር....ለሀገሩ የመጀመሪያ ግቡን ያገባው በክሮሺአ 3ለ2 ሲሸነፉ ነበር....
★★★★★★★★★★★★★★★★★★★★★
ክፍል አንድ ተጠናቀቀ ክፍል ሁለት ይቀጥላል
ላይክና ሼር ማድረግ አያስከፍልም፡፡ለወዳጅ ጓደኛዎ ሼር ያድርጉት፡፡በቀጣይ የሌሎች ከዋክብቶችን የህይዎት ታሪክ ይዘንላችሁ እንቀርባለን፡፡
★★★★★★★★★★★★★★★★★★★★★

Pages: 1