ሄሎ ሀበሻ ምርጥ የሀበሻ መዝናኛ ሰፈር፣
ይህ ዌብ ሳይት ሀበሻን ከመላው አለም በማገናኘት የሚያወያይ
የሚያዝናና ዌብ ሳይት ወይም መድረክ ነው፥፥
ተሳተፉ ፣ ኮመንት አድርጉ ፣ የራሳችሁን ፃፉ
0 users browsing Cooking & Recipes . | 1 guest
Pages: 1
Posted on 07-16-17, 04:30 am


Karma: 100
Posts: 86/95
Since: 08-19-16

Last post: 403 days
Last view: 403 days
ባህላዊ ወፍጮ
------------
ባህላዊ ወፍጮ ከድንጋይ ዘር ይሰራል

ለወፍጮ መስሪያ የሚመረጥ ድንጋይ በቀላሉ የማይፈረፈር የድንጋይ ዘር ሆኖ በባለሙያ የተመረጠ መሆን አለበት ምክንያቱም ሲፈጭበት እና ድንጋዩ ከጥሬ ዕቃው ጋር ሲፋተግ እየተፈረፈረና እየደቀቀ እንዳያበላሽ ነው::

ወፍጮው ሁለት ክፍል እና ስም አለው

1. ወፍጮ
2. መጅ ተብሎ ይጠራል

ወፍጮ በሁለት መንገድ ይሰራል

1. ዝርግ
2. ጎድጎድ ያለ

ዝርጉ ሲሰራ ከአንድ በኩል ቀጠን በሌላው በኩል ወፈርና ዘቅዘቅ ብሎ በድንጋይ መዶሻ ተጠርቦና ተስተካክሎ በባለሙያ ይሰራል

ጎድጎድ ያለው መለንቀጫ፣መዳጫ ወይም መዶቆሻ ይባላል

እርጥብ የሆኑ ጥሬ ምግቦችን ለመለንቀጥ የሚጠቅም ስለሆነ እንዳያፈስና ለመፍጨት እንዲመች ሆኖ ዙሪያው ቀልበስ ተደርጎ ይሰራል

ለሁለቱም ወፍጮ በእጅ ለመያዝ እንዲመች ተደርጎ እንደወፍጮው መጠን መጅ ይሰራለታል

ወፍጮውንና መጁን አንድ ላይ በማፋጨት መስተካከሉ ከተረጋገጠ በኋላ የወፍጮው ጠርስ እንዳይሟልጭ በመዶሻ ወይም ሹል በሆነ ድንጋይ ይወቀራል

ብዙ በተሰራበት ቁጥር ወፍጮው ሊሟልጭ ሊለሰልስ ይችላል

ከሟለጨ ሊከካ፣ሊገረድፍ፣ሊፈጭ፣ሊሰልቅ፣ሊነለቅጥ ወይም ሊደቁስ ስለማይችል በሟለጨ ቁጥር መወቀር ወይም ወፍጮውም መጁም መሻከር አለበት

በዚህ መልኩ ከተያዘ ለብዙ አመታት የሚያገለግል ባህላዊ መሳሪያ ነው

አጠቃቀም
---------
1. ወፍጮውንና መጁን ማጠብና ማድረቅ
2. መሬት ላይ ክስር ምንጣፍ በማንጠፍ እንዳይነቃነቅ ከጎንና ጎኑ ትንሽ ድንጋይ ማጉረስ

የሚፈጨውን እህል ዱቄት የሚያርፍበት ዕቃ ከወፍጮው ፊት ትንሽ ከተት ወይም ወደ ወፍጮው ጠጋ አድርጎ ማስቀመጥ ከዛም የሚፈጨውን ማቅረብ

ጉልበት እንዳያም ለጉልበታችን የጨርቅ ትራስ ማዘጋጀት

በመቀጠል በጉልበት ተንበርክኮ በትንሽ በትንሹ እየቆነጠሩ ከመጁ ኋላ በማስውቀመጥ መጁን ወደፊት ወደ ኋላ እያደረጉ በሁለት እጅ ይዞ እንደአስፈላጊነቱ መፍጨትና ማድቀቅ ፣መንፋት የሚለነቀጠውንም ለመለንቀጥ እንዲመች አድርጎ መለንቀጥና መጨረስ ከዛም በንጹህና ክዳን ባለው ዕቃ ደረቅና ቀዝቃዛ ቦታ በማስቀመጥ መጠቀም ይቻላል

2ኛ ወፍጮውን በመትከል ነው

ይህ በእንብርክክ ከመፍጨት የተሻለ ዘዴ ነው ይኸውም በፈጪው ቁመት መጠን ጎንበስ ተብሎ እንዲፈጭ በመገመት ወፍጮው በድንጋይ፣በቦካ ጭቃና ጭድ ይሰራል ከፊት ለፊቱም ለተፈጨው ማስቀመጫ ይሰራለታል በየጊዜው በእበት ይለቀለቃል

በአብዛኛው ከቤት ግድግዳ ጋር ተጣብቆ ይሰራል ይህ ተንበርክኮ ከመፍጨት የተሻለ ነው

ስለ ወፍጮና ሙቀጫ ስለ ጥጥ ፈትል ሲነሳ እንዲሁም ውሃ ከምንጭ በእንስራ መወገብ ስለመቅዳት ሲታሰብ የጥንት ሴቶች ምን ያህል ስራ እየሰሩ እንዳለፉና ተፈጥሮ የለገሳቸውን ማርገዝ፣መውለድ(ማማጥ) ማሳደግ በአብዛኛው ስራ በሴት ጫንቃ ላይ ሆኖ እንዳለፈ ይታየኛል አንረሳቸውም እንወዳቸዋለን
ለደረስንበት ቴክኖሎጂ መሸጋገሪያ ድልድዮቻችን ናቸው


Pages: 1