ሄሎ ሀበሻ ምርጥ የሀበሻ መዝናኛ ሰፈር፣
ይህ ዌብ ሳይት ሀበሻን ከመላው አለም በማገናኘት የሚያወያይ
የሚያዝናና ዌብ ሳይት ወይም መድረክ ነው፥፥
ተሳተፉ ፣ ኮመንት አድርጉ ፣ የራሳችሁን ፃፉ
0 users browsing Medical Innovations. | 1 guest
Pages: 1
Posted on 06-01-17, 04:19 am


Karma: 90
Posts: 400/879
Since: 02-29-16

Last post: 34 days
Last view: 34 days
የ2016 በህክምና የኖቤል ተሸላሚ
ጃፓናዊው ተመራማሪ ለሽልማት የበቁት «አውቶፈጊ» በተሰኘው ምርምራቸው ነው። አውቶፈጊ፦ ስያሜው ከግሪክ የተገኘ ሲሆን፤ ሁለት ቃላትን ማለትም ራስን በራስ (Auto) እና መብላት (phagein) የተሰኙን ቃላት ያዋቀረ ነው። ጃፓናዊውን ተመራማሪ ለሽልማት ያበቃቸው ጥናት ሕይወት ያላቸው ፍጡራን ደቂቅ፥ ረቂቅ ክፍል ማለትም ኅዋስ (Cell) ራሱን በራሱ እንዴት እንደሚበላ ይቃኛል። የፍጡራን ኅዋስ ራሱን በራሱ የሚበላው መቼ እና ለምን ይኾን?
በጃፓን የቶኪዮ የሥነ ቴክኒክ ተቋም የፍጥረታት ኅዋስ ጥናት ተመራማሪው ዮሺኖሪ ዑሱሚ በህክምናው የሣይንስ ዘርፍ የዓለማችን ከፍተኛውን ሽልማት አሸንፈዋል። ስቶኮልም የሚገኘው የኖቤል ሽልማት ኮሚቴ ጃፓናዊው ተሸላሚ የሆኑት የሰውነት ሴል ከፊል ራሱን በራሱ የሚበላበት «የአውቶፈጊ አሠራር ላይ» ላበረከቱት ግኝት ነው ብሏል። ኅዋስ ከፊል ራሱን በራሱ የሚበላበትን ኹነት ማጥናት በተለይ በነቀርሳ አለያም በነርቭ ኅመም ለሚሰቃዩ ሰዎች የሚኖረው አስተዋጽዖ ላቅ ያለ ነው። የካሮሊንስካ ተቋም የኖቤል ኮሚቴ ጸሐፊ ቶማስ ፔርልማን።
«በካሮሊንስካ ተቋም የኖቤል ኮሚቴ በህክምናው ዘርፍ የዘንድው የ2016 የኖቤል ሽልማት የአውቶፈጊ አሠራር ላይ ላበረከቱት አስተዋጽዖ ለዮሺኖሪ ዑሱሚ እንዲሰጥ ዛሬ ወስኗል።»
በህክምና ዘርፍ የኖቤል ተሸላሚ፥ ጃፓናዊው ዮሺኖሪ ዑሱሚ
ዘንድሮ የኖቤል ኮሚቴው በህክምናው ዘርፍ የኖቤል ሽልማቱን ለአንድ ግለሰብ ብቻ ነው የሰጠው። ባለፉት ዓመታት የተመራማሪዎችን ሥራ ማበላለጡ እጅግ አዳጋች ስለሚሆንበትም ኮሚቴው ሁለት አለያም ለሦስት ሰዎች በጋራ ነበር በዘርፉ የኖቤል ሽልማት የሚያበረክተው። ዘንድሮ የጃፓናዊው የምርምር ሥራ ላይ የሚደርስ አልተገኘም እንደ ኮሚቴው ማብራሪያ። የዮሺኖሪ ዑሱሚ ግኝት እጅግ በመላቁም ብቸኛው ሎሬት ሆነው ተመርጠዋል። ለዘመናት የምርምር ልፋታቸው ከፍተኛውን ዕውቅና ያገኙት የ71 ዓመቱ አዛውንት ተመራማሪ ተሸላሚ መሆናቸው ከተነገራቸው በኋላ ጃፓን መዲና ቶኪዮ ውስጥ ንግግር አሰምተዋል።
«እንደተመራማሪ በእርግጥም ከዚህ የላቀ አንዳችም ክብር የለም። ባለፉት ዓመታት በርካታ ሽልማቶችን ለመቀበል ታድያለሁ። ሆኖም የኖቤል ሽልማት ለየት ያለ ግዝፈቱ ይሰማኛል።»
ጃፓናዊውን ለሽልማት ያበቃው አውቶፈጊ የተሰኘው ምርምር የሰውነት ኅዋስ ከፊል ራሱን በራሱ በመመገብ የተለያዩ በሽታዎችን ለማጥቃት ይረዳል። ለአብነት ያህል፦ የሚያንቀጠቅጥ የነርቭ ኅመም፣ የአዕምሮ ዝንጉነት እና የስኳር በሽታዎችን ለመዋጋት ይጠቅማል።
በእርግጥ የአውቶፈጊ ጥናት ዘርፍ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቀው ከግማሽ ምዕተ-ዓመት በፊት የዛሬ 56 ዓመት በፊት ነው። ሆኖም የጥናት ዘርፉ ወደር ያልተገኘለት እመርታ በማስመዝገብ በ1990ዎቹ ከፍተኛ ትኩረት እንዲያገኝ ያስቻሉት ጃፓናዊው ሣይንቲስት ናቸው።
እጅግ ደቃቃ በሆነ አካላት እና የመድኃኒት ግኝት ላይ ጥናት የሚያከናውነው በርሊን የሚገኘው የጀርመኑ የላይብኒትስ ተቋም ባልደረባ ፎልከር ሐውከ የጃፓናዊው ተመራማሪ የጥናት ሥራ ለበርካታ ምርምር ፈር ቀዳጅ መሆኑን መስክረዋል።
«ዮሺኖሪ ዑሱሚ ጥልቅ ምርምር ማድረግ ከመጀመራቸው አስቀድሞ የነበሩ የጥናታዊ ጽሑፍ ኅትመቶችን ብትመለከት በጣም ጥቂት ነበሩ። አብዛኛው ጥንታዊ ጽሑፍ እንደውም በሳቸው የቀረቡ ናቸው። እናም እሳቸው አጥብቀው የያዙት ምርምር እጅግ ወሳኝ መሆኑ ሲታወቅ በርካታ ተመራማሪዎች ትኩረት መስጠት ጀምረዋል። ከዚያን ጊዜ አንስቶም አውቶፈጊን የሚመለከቱ በሺህዎች የሚቆጠሩ ጥናታዊ ጽሑፎች በየዓመቱ እየወጡ ነው። ስለዚህ መሠረታዊ ሣይንስ በአንድ ግለሰብ አለያም ቢያንስ በአንድ ቤተ-ሙከራ እንዴት ሊነቃቃ እንደሚችል ድንቅ ምሳሌ ነው። በእርግጥም ምርምሩ አዲስ መንገድ ማመላከት ችሏል።»
ጃፓናዊው ዮሺኖሪ ዑሱሚ ስለ አውቶፈጊ ከማንም ቀድመው ጥልቅ ጥናት ማድረግ የጀመሩት ቀለል ባለ መንገድ እርሾ ውስጥ የሚገኙ ኅዋሳትን በመገንዘብ ነበር። እርሾ ውስጥ የሚገኙ ኅዋሳት ጥናት የሰው ልጅ ኅዋሳት ጥናት ማሳያ ተደርጎ ብዙውን ጊዜ ይወሰዳል። ምርምሩም ቀላል እንደሆነ ነው ሳይንቲስቶች የሚገናገሩት።
ገና ከመጀመሪያው ግን ዮሺኖሪ አስቸጋሪ ነገር ገጠማቸው። እርሾ ውስጥ የሚገኙ ኅዋሳት በአጉልቶ ማሳያ መነጽር የማይታዩ እጅግ ደቂቅ መሆናቸው የምርምሩ ቀዳሚ መሰናክል ነበር። እናም ኅዋሳቱ ከፊል ራሳቸውን በራሳቸው የሚበሉ (autophagy) ስለመሆናቸው እርግጠኛ መሆን አልቻሉም። መሰናከሉን ግን ተመራማሪው በተለየ ዘዴ አለፉት።
ጃፓናዊው ተመራማሪ የተሸለሙበት የጥናት ዘርፍ፥ «አውቶፈጊ»
ከኅዋሳቱ ውስጥ ኢንዛይም ነቅሶ በማውጣት የእርሾው ኅዋሳት እንዲርባቸው አደረጉ። በቅጽበት ውስጥም ኅዋሳቱ በሕይወት ለመቀጠል ከፊል ራሳቸውን ሲበሉ መመልከት ቻሉ። ፕሮፌሰር ማሪያ ማሱቺ በካሮሊንስካ ተቋም የሞሎኪውል ባዮሎጂ እና የኅዋሳት ጥናት ፋኩልቲ ውስጥ የተሐዋሲ ተመራማሪ ናቸው። የጃፓናዊው ተመራማሪን የጥናት ውጤት እንዲህ ያብራራሉ።
«የሰውነታችን ኅዋሳት ከፊል ራሳቸውን በመብላት እና እራሳቸውን በማደስ ረሐብ አለያም ሌሎች ጭንቀት አምጪ ነገሮችን እንድንቋቋም ያስችሉናል። ሰውነታችንን የሚወሩ ተሐዋሲያንን እና ባክቴሪያዎችን እየለቀሙ በማጥቃት ሰውነት ምርቀዛ እንዳይከሰትበት ይከላከላሉ። በኅዋሳቶቻችን ውስጥ የተጎዱ ፕሮቲኖችን በማስወገድም ከፊል ራሳቸውን በመመገብ ኅዋሳት እንዲታደሱ እገዛ ያደርጋሉ።»
የአውቶፈጊ የምርምር ዘርፍን ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም ያስተዋወቁት ቤልጅጋዊው ሳይንቲስት ክርስቲያን ደ ዱቭ ናቸው። ሣይንቲስቱ ሕይወት ባላቸው ነገሮች ላይ የሚገኝ የንጥረ ነገር ቅንብር ማለትም ባዮኬሚስትሪ ያጠናሉ። አውቶፈጊን ያስተዋወቁት እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1960ዎቹ ነበር። በ1974 ዓመተ ምኅረትም ለላቀ የምርምር እገዛቸው በህክምና የኖቤል ተሸላሚ ሆነዋል።
ከዚያን በኋላ ግን ለቀጣዮቹ ዐሥርተ ዓመታት በአውቶፈጊ ዘርፍ ፍላጎት ያሳየ ተመራማሪ አልታየም። ጃፓናዊው ዮሺኖሪ ዑሱሚ አዲስ የላቀ ግኝት ይዘው ብቅ እስኪሉ ድረስ ማለት ነው። ኅዋሳት በረሀብ ወቅት እና ሰውነት በበሽታ በሚጠቃበት ጊዜ እንዴት ራሳቸውን በራሳቸው በከፊል እየበሉ መዝለቅ ስለመቻላቸው አጥጋቢ ትንታኔ በመስጠታቸውም ጃፓናዊው ተመራማሪ ለሽልማት በቅተዋል።
የኖቤል የሽልማት ኮሚቴ ትናንት በፊዚክስ ዘርፍ የቁስ ኢ-ይዘታዊ ቅርጽ የባሕሪ ሽግግር (topological phase transitions ) እና የቁስ ኢ-ይዘታዊ ባሕሪ (topological phases of matter ) ላይ የላቀ እመርታ ያሳዩ ሦስት የፊዚክስ ጠቢባን አሸናፊ መሆናቸውን ገልጧል። ዴቪድ ጀይ ቱለስ፣ ኤፍ ዳንካን ኤም ሀልዴን እና ጄይ ማይክል ኮስተርሊትዝ የጎርጎሮሳዊውን የ2016፤ የኖቤል የፊዚክስ ሽልማት አሸናፊ መሆናቸው ተገልጧል።
ሰኞ ዕለት በህክምናው ዘርፍ ጀምሮ ማክሰኞ የፊዚክስ ተሸላሚዎችን ያስተዋወቀው የኖቤል ሽልማት እስከ ዐርብ ድረስ ይዘልቃል። ዛሬ የኬሚስትሪ ዘርፍ ተራ ሲሆን፤ ዐርብ የሰላም ተሸላሚው ይታወቃል። የፊታችን ሰኞ በኢኮኖሚ ዘርፍ ተሸላሚ ማን እንደሚሆን ይገለጥና ሦስት ቀን ቆይቶ ሐሙስ የስነጽሑፍ አሸናፊው ማንነት ይነገራል።
ስቶኮልም ስዊድን ተወልዶ፣ ሩስያ አድጎ ፈረንሳይ እና ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ እንደተማረ በሚነገርለት አልፍሬድ ኖቤል ስያሜ የተሰጠው የኖቤል ሽልማት አሰጣጥ ሥነ-ስርዓት እጎአ ታህሳስ ዐስር ቀን፤ 2016 ዓ.ም በስቶክሆልም ከተማ ይካሄዳል። ለእያንዳንዱ ተሸላሚ 930,000 ዶላር፣ የክብር ሜዳይ እና ዲፕሎማም ተዘጋጅቷል።
Pages: 1