ምርጥ የሀበሻ መዝናኛ ሰፈር፣ ኑ እና የምትሉትን በሉ!
ይህ ዌብ ሳይት ሀበሻን ከመላው አለም በማገናኘት የሚያወያይ
የሚያዝናና ዌብ ሳይት ወይም መድረክ ነው፥፥
0 users browsing Music. | 3 guests
Pages: 1
Posted on 04-15-17, 09:11 pm


Karma: 100
Posts: 205/425
Since: 07-12-15

Last post: 72 days
Last view: 72 days
የብላቴናው ከፍታ!
«ዘውድአለም ታደሰ»

የቴዲን ዘፈን አለመውደድ ይቻላል። ነገር ግን ዘፈኑን አልወደድኩትም ብሎ ማብቃት ሲቻል አላስፈላጊ ዘለፋ ውስጥ መግባት ችግሩ ከዘፈኑ ሳይሆን ወይ ከዘፋኙ ወይ «ኢትዮጵያ» ከሚለው ስም ነው እንድንል ያደርገናል!

ወዳጄ! እኔ በግዲ ከቴዲ የሚስረቀረቅ ድምፅ ወይም የሙዚቃ ጥበብ ጠብቄ አላውቅም። በርግጥ በርሱም አይታማም ግን እኔ ከሱ ምጠብቀው «ቃል» ነው! በምን ቅኝት ዘፈነ ሳይሆን ምን ብሎ ዘፈነ? ነው ምለው። ቴዲ ከዘፋኝነት አልፎ የፍቅርና የአንድነት ድልድይ ሆኗል! ይህን ክብር የሰጠው ህዝብ ነው! እንግዲህ ምንም ማድረግ አይቻልም!

ስማኝ ዘመዴ! ብዙዎች በተዋበ ድምፅና ዜማ ፣ በጥኡም ግጥም ስለሐገር ዘፍነዋል። እግዚሃር ይስጣቸው! ነገር ግን አንድ ነገር ልጠይቅህ እስቲ ..... ንፁህ የኢትዮጲያዊነት መንፈስ ሲዘፈን ሰምተህ ታውቃለህ? ከልብ የሚፈልቅ የሐገር ፍቅር ሲዘፈን ሰምተህ ታውቃለህ? ኢትዮጲያን በአራቱም አቅጣጫ ባርኮ የሚጨርስ ዘፈን ሰምተህ ታውቃለህ?

በናቱ ፍቅር እንደተለከፈ ህፃን የናቱን አዳፋ ቀሚስ ጨብጦ ከኋላ ከኋላዋ እየተከተለ «ደሃም ብትሆኚ ፣ በጉዲፈቻ ሊያሳድጉኝ የሚችሉ ብዙ እናቶች ቢኖሩም ፣ የተሻለ ህይወት የመኖር እድሉ ቢኖረኝም ፣ እናት ነሽና ከስርሽ ወደየትም አልሄድም!» ብሎ የዘፈነ ሰው አይተህ ታውቃለህ?

ልጁ «ጠላቶችሽ በጫሩት እሳት ራሳቸው ይነድዳሉ» ሲል አድዋን አላሰብክም? ጥቁር ራሱን እንደሰው በማይቆጥርበት ዘመን አባቶቼ በምን ተአምር ጣሊያንን ድል አደረጉ? ብለህ አልጠየቅህም? ዚያድ ባሬ እሳቱን ጭሮ ፣ታንኩን አሰልፎ ፣ ወታደሩን አስታጥቆ ፣ በአፍሪካ ከፍተኛ የተባለውን ጦር ይዞ ፣ ድንበርህን ሲሻገር አባቶችህ በምን ተአምር አሳፍረው መለሱት? ነጭ ቢሆን ጥቁር ፣ ከሩቅ መጣ ከቅርብ ፣ ከየትም ይምጣ ከየት ኢትዮጲያን ሊያቃጥል እሳት የለኮሰ ሁሉ በእሳት ይጠፋል። «ሰይፍን የሚያነሱ በሰይፍ ይጠፋሉ» እንዲል ቃሉ። ይህን በሁለት መስመር ግጥም ነግሮኝ ነው እንደታይም ማሽን ወደኋላ መልሶ አባቶቼ እግር ስር የጣለኝ!

ስማኝማ ዘመዴ .... ዛሬ ላይ ቆሞ የኢትዮጲያን ውድቀት ማውራት ቀላል ነው። ዛሬ ላይ ቆሞ ክስረታችንን መከተብ ቀላል ነው። ምክኒያቱም የምናየውና የምንሰማው ነገር ሁሉ ተስፋ ያስቆርጣል። ..... ነገር ግን ይህ የናቱን አዳፋ ቀሚስ በእጆቹ ጨብጦ የሚከተል ህፃን በናቱ የቀሚስ ቀዳዳ አጮልቆ ሰማዩን በተስፋ እያየ ... እንዲህ በማለት ነገዋን ይተነብያል!
«በሰማዩ ላይ ፥ ቢታይ ቀለም
የሷ ነው እንጂ ፥ ሌላ አይደለም
የመጭው ዘመን ፥ ፊት ናት መሪ
ዛሬ አለም ቢላት ፥ ኋላ ቀሪ!»

ይሄ ከፍታ አይደል? ይሄ ክብር አይደል? ይሄ የትውልዱ ድምፅ አይደል? ይሄ ትንቢት አይደል? ከዚህ በላይ ምን ይዘፈን? ከዚህ በላይ ምን አይነት ቃል ይምጣ? ሁፍፍፍፍ!!!

«በሰሜን በደቡብ
በምስራቅ በምራብ ላይ
ሙሉ ይሁን ያንቺ ሲሳይ!»

ብላቴናው መልእክቱን ሚያሳርገው ሐገሩን በአራቱም አቅጣጫ በመባረክ ነው! ዘር ከዘር ፣ ብሔር ከብሔር ፣ በሚነካከስበት በዚህ የተኩላ ዘመን ልጁ እጆቹን ከፍ አድርጎ ሁሉንም በእኩል ፍቅር እየተመለከተ ፣ በአራቱም አቅጣጫ በረከትን ከአርያም ይጠራል!

አማራው ይባረክ! ኦሮሞው ይባረክ! ትግራዩ ይባረክ! ደቡቡም ይባረክ! ኤርትራም ትባረክ! ሶማሌም ትባረክ! አፋሩም ይባረክ! በኢትዮጵያ ምድር ላይ የሚኖር የትኛውም ፍጡር ይባረክ! አዝመራው ፣ ተራራው ፣ ወንዙና ባህሩ ሁሉ ይባረክ! ኢትዮጲያን የሚባርክ ሁሉ ይባረክ! ስለኢትዮጲያ ቀናውን የሚያስብ ሁሉ ይባረክ! ኢትዮጲያን የሚወድ ሁሉ ይባረክ! አፈሯን የረገጠና ውሃዋን የቀመሰ ሁሉ ይባረክ!

ብላቴናውም ይባረክ!!

Pages: 1