ሄሎ ሀበሻ ምርጥ የሀበሻ መዝናኛ ሰፈር፣
ይህ ዌብ ሳይት ሀበሻን ከመላው አለም በማገናኘት የሚያወያይ
የሚያዝናና ዌብ ሳይት ወይም መድረክ ነው፥፥
ተሳተፉ ፣ ኮመንት አድርጉ ፣ የራሳችሁን ፃፉ
0 users browsing Movies. | 1 guest
Pages: 1
Posted on 03-25-17, 05:34 pm


Karma: 100
Posts: 11/769
Since: 03-20-17

Last post: 375 days
Last view: 375 days
ዘመን ድራማና ርካሽ ገጸባህሪያት – (ቃልኪዳን ኃይሉ)

ዘመን ድራማ ሊጀምር ሲል በጉጉት ሲጠብቁት ከነበሩት ሰዎች ውስጥ አንዱ እኔ ነኝ፡፡ ሰው ለሰው ድራማን ከተወኑትም ሆነ ከጻፉት ውስጥ አንድ ሳይጎል አሉበት ባይባልም ከተዋንያን እስከ ደራሲ አብዛኞቹ ሰዎች ዘመን ላይ ስለሚገኙ እንዲሁም የተሻለ አቅምና ብቃት እንዳላቸው ሰው ለሰው አስመስክረው ስለነበረ ዛሬ ዘመን ላይ ከፍ ያለ ነገር በጉጉት መጠበቄ አመክንዮዋዊ ነው፡፡እንደተጠበቀውም በሀገራችል ለመጀመሪያ ጊዜ በሳምንት ሁለቴ፤ ከፍ ባለ የካሜራና የዝግጅት ጥራት፣ በተሻለ የተዋንያን ችሎታና አቅም በኢትዮጵያ ድራማ ላይ ዳግም ተከሰቱ፡፡ የኔ ብቻ ሳይሆን የብዙ ኢትዮጵያውያን ጉጉት ቃና ሙሉ ለሙሉ ያለተቀናቃኝ የተቆጣጠረውን የተከታታይ ድራማ ሜዳ የአቅሙን ያህል ተጋፍቶ ተመልካችን ወደ ሀገር ቤት ሜዳ ይመልሳል ተብሎ የተጠበቀ ድራማ ነው ዘመን፡፡
.
እንደኔ እይታ ይህ ነገር በመጠኑም ቢሆን ዘመን ድራማ አሳክቷል፡፡ ነገር ግን ለሰላሳ ምናምን ክፍል የሄደው ዘመን ድራማ እስከአሁን ድረስ እኩይ ገጸባህሪ እንጂ ነጥሮ የወጣ ይህ ነው የሚባል መልካም ገጸ ባህሪ ያላየንበት፤ የኢትጵያን ሕገ መንግስት ይመስል ብሔረ ብሔረሰቦችንና ቋንቋቸውን፤ ዘዬና አነዋወራቸውን ካልነካካሁ፤ መቼቴን በየሀገሪቱ ክልሎችና ከተሞች ካላደረኩ የሚል ሆነብኝ፡፡
.
እውነት ነው አንድ ተከታታይ ድራማ ሁሉን ማሕበረሰብ አቅፍ ታሪክ ቢኖረው ለተቀባይነቱ ሆነ ሁሉን ተደራሽ ከማድረግ አንጻርም መልካም ነው፡፡ ይሁን እንጂ ጥበብ በግድ ጠምዝዞ አንድም የብሔር ብሔረሰብ ሰፈር እንዳይቀር ካልን፤ አንድም ብሔር ብሔረሰብ ቋንቋውና ባሕላዊ ጨዋታው እንዳይቀር ስንል፡፡ በዙ የሚቀሩ ብሔረሰቦች፣ ባህሎቻቸው እና አመለካከቶቻቸው አሉ፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያውያን ነገዶች ሕገ መንግስቱ ላይ የተጻፉት ዘጠኙ ብቻ ስላልሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ ሌሎች ቅር እንደሚላቸው ግልጽ ነው፡፡
.
ግን ገጸ ባህሪ ላይ ያሉ ሰዎች የመላው ኢትዮጵያውያን ልጆች እንጂ የአንድ ክልል ልጆች ብቻ ናቸውን? ታሪኩስ ግዴታ ባህርዳር፣ ሞያሌ፣ ወሎ፣ ሐዋሳ… የሚባሉ ከተሞች ስለረገጠ ብሔር ብሔረሰቦችን ተደራሽ አድርጓልን? ወይስ በትክክል ያ ገጸ ባህሪ ለጻፍነው ታሪክ ከዚያ አካባቢ ስለሚያስፈልገን ነው መግባት ያለበት ወይም የገባው?

ዘመን ድራማ ሴቶች
በዘመን ድራማ አንድም ነፍስ ያላት (ሕያውነቷን ማጠየቄ አይደለም)፣ የኔ ጀግና፣ የኔ ሞዴል የምላት ሴት አላየሁም፡፡ የዘመን ድራማ ሴቶች ሕይወትን ሆና ከምትተውነው የጸደይ ገጸ ባህሪና ከሩታ መንግስተ አብ በስተቀር ሌሎቹ ገጸ ባህሪዎች አመክንዮ የሚባል ነገር የማያውቁ፣ ራስ ወዳዶች፣ ክፋት የሞላቸው፣ ወሲብ ጥማት ከእግር ጥፍራቸው እስከ ራስ ጸጉራቸው ድረስ ወጥሮ የያዛቸው (አዳነችና ጓደኞቿ፣ አቡሽ የሚያገኛቸው ሹገር ማሚዎች በይበልጥ፣ የሳምሶን ቤቢ ሚስት ሆና የምትተውነው ገጸባህሪ)፣ ጠንካራና ጀግና መስለው ግን በቀላሉ የሚሸወዱና የሚታለሉ (የሩታ መንግስተአብ ገጸባህሪ) አይነት ናቸው፡፡
.
እነዚህ ሁሉ እኩይ ገጸ ባህሪዎች አይኑሩ አይደለም ይኑሩ ግን ትውልዱ ሞዴል የሚያደርገው፤ ተመልካቹ በፍቅር የሚወደው ሚናውን የለየ አንድ ድንቅ ሴት፤ አይበገሬ፣ ማንም እየተነሳ እንደቤተክርስቲያን ደጃፍ የማይስማት፣ ማንም ዝም ብሎ እንዳሻው ሲፈልግ የማያቅፋት፤ ማንም ሲፈልግ የማይገፋት ሲፈልግ የማይጎትታት ጠንካራ ገጸበህሪ ከዋና ተዋንያኖች ውስጥ እንዴት ይጠፋል?
.
ኢትዮጵያውያን ሴቶች እኮ ዘመን ድራማ ላይ እንደምናያቸው ጠባቂ እንደሌላው ማሳ ማንም የሚዘግናቸው አይደሉም አልነበሩም፡፡ ኢትዮጵያውያን እንስቶች ከእውቀት ይልቅ ወቅታዊ ፊልምና ሙዚቃ የሚንጣቸው፣ ከጥሩ ፍቅር ይልቅ ፍቅረ የተባለ ባለሀብት የሚያስደነግጣቸው፤ ከንፈራቸውን ለአንድ ብርጭቆ ወይን ገላቸውን ለብርጭቆ ውስኪ የሚገብሩ፤ በሌላቸው ብር ተበድረውና ተለቅተው ፎርጂድ ጫማና ልብስ ገዝተው ሰው ሰፈር ሄደው እዩኝ ብቻ የሚሉ እንስቶች ያሉባት አይደለችም፡፡ ኢትዮጵያውያን እንስቶች ስንል እኮ ያቺ
ኢየሱስ በወንጌል የመሰከረላት ጥበብን ሽታ ከአክሱም ወደ ኢየሩሳሌም የተጓዘች በመጨረሻው ቀን ለፍርድ የተመረጠችው ንግስተ ሳባ የተወለደችበት፤ እነዚያ ጠላትን አላስቀምጥ ያሉ የሴት አርበኛ ሸዋረገድ ገድሌ፣ የእቴጌ ጣይቱ ብጡል ሀገር ነች፡፡
.
ድራማችንም ላይ እነዚህን ሴቶች ዳግም እንፈልጋለን፡፡ ዛሬም እንደነዚህ አይነት ጀግና ለሀገርም ለዓለምም የሚበቁ እንስቶች እንፈልጋን እንጂ በዓመት አንዴ የሴቶች ቀን እያከበሩ የተቀሩትን ሶስት መቶ ስልሳ አምስት ቀኖች አሲድ እየደፉ፣ በአደባባይ በጥይት እየተኮሱ፣ እንደ አውዳመት በግ የእንስት አንገት እየበጠሱ፣ በቆንጆ ሴት ፊት ላይ አሲድ እየደፉ፣ ሴትን ልጅ በቡድን እየደፈሩ… ኅብረተሰብ አይገነባም፡፡
.
ከመገናኛ ብዙሐንም ድራማዋቻችን በዚህ ጉዳይ ተጠያቂ መሆናቸው አይቀሬ ነው፡፡ ለሴት ልጅ በጣም የወረደ ገጸ ባህሪ ሰጥቶ፣ ኅብረተሰቡ ሴት ማለት ደካማ፣ ከንቱ፣ ማንም እስከፈለገ ድረስ እንደ ሬስቱራንት ምግብ ቴክአዌይ የሚያደርጋት ዋጋው ካልሆነ በስተቀር የትኛዋም የምትሸጥ አድርጎ መሳል ነው፡፡
.
መግዛት ወይም ማግኘት ያቀተው ደግሞ የሚያርዳት፣ ካልሆነም የሚደፍራት ካልሆነም አሲድ የሚደፋባት ከንቱ ፍጥረት ሆና እየተሳለች ነው፡፡ የድሮ ኢትዮጵያውያን ሴትን ከድንግል ማርያም ወይም ከመሪማ ጋር አመሳስለው በመቅረጽ የሚያከብሩና ትልቅ ቦታ የሚሰጡ ነበሩ፡፡ የአሁኑ ሰለጠንኩ ባይ ትውልድ ደግሞ ሴት ከወሲብና ወሲብ ብቻ ጋር የሚያይ ነው፡፡ እድሜ ለዘመን መሰል ድራማዎች፡፡
.
ወሲብና ዘመን ድራማ
.
ወሲብ እንደ ዘመን ድራማ ቀላል የሆነበት ሀገራዊ ድራማ አላየሁም፡፡ የአሜሪካና የአውሮፓ የቤተሰብ ፊልሞች እንኳ አንድ ሁለቴ ራት ከበሉ በኋላ የሚሆን ቢሆንም ዘመን ድራማ ላይ ግን ወሲብ ቀላል ነገር ነው፡፡ ይህ ደግሞ በአባላዘር በሽታ፣ ኤች አይቪ እንዲሁም ሔፕታይተስ በተባለ ልቅ በሆነ የወሲብ ምክንያት የሚመጡ በሽታዎች በስፋት ያለባት ሀገር
ውስጥ ዘመን ላይ እነዚህ ነገሮች የሌሉባት ያክል ባለትዳሮች እየወሰለቱ፤ ወጣት ወንዶች አሮጊት ወንዶች እያነፈነፉ ወሲብ የሚፈጹምበት ነው፡፡
.
ኢትዮጵያውያን አላህን ወይም እግዚአብሔርን የምናምን ነን፡፡ ስለዚህ ክርስትናም ሆነ እስልምና ዝሙትን አጥብቆ ይከለክላል፡፡ ከዚያ ከፍ ያለ ከአንድ በላይ የወሲብ ጓደኛ መያዝ ግን አጥብቆ የተከለከለ ብንፈልግ እንኳ ያደግንበት ማኅበረሰባዊ ወግና ስርአት ሳናስበው ወደ አእምሯቸውን እየመጣ ህሊናችንን ጠቅ የሚያደርገን ነን፡፡
.
ዘመን ድራማና ገጸባህሪዎቹ ግን ይገርማሉ፡፡ በይበልጥ አቡሼ እንዲሁም የአዳነች ተቀናቃኝ ገጸባህሪ ስሟ ጠፋኝ ብቻ እሷ፤ እራሷ አዳነች (ሃና ዮሐንስ)… ከማንም ጋር የሚጋደሙ ወሲብን በየቀኑ ፊት እንደመታጠብ ያዩ ትውልዱም ቀለል አድርጎ እንዲያየው የሚገፋፉ በመጥፎ ገጸ ባህሪያቸው የሚያስተምሩ ናቸው፡፡
.
የሳምሶን ቤቢ ሚስት በበቀል አሳባ ወሲብ የምትፈጽም፤ የጓደኛዋን ባል የምታማግጥ፤ በራሷ ባል ላይ በደል የምትፈጽም ውሸታም ሴት ነች፡፡ ሩታ መንግስት አብ (ገጸባህሪዋን ማለቴ ነው) ለስሙ ጥሩ ባህሪ አላት የምትባል ግን ሊቆጣጠሩት የማይችሉት ቅናት ውስጧን የተቆጣጠራት ፤ እሷ ባሏን ከሌሎች ሴቶች ጋር አትስራ እያለች እሷ ግን ገና ለገና በስልኬ እየደወለ አስቸገሮኛል ያለችው ወንድ፤ የአዞ ይሁን የራሱ እንባ ባልታወቀ
ነገር አነባ ተብሎ የምትሳም ገጸባህሪ ነች።
.
ድራማው ላይ አለች የምትባለው ‘ጀግና’ ገጸባህሪ ሕይወቴ (ጸደኒያ) ቅን አሳቢ፣ ለጠላቶቿ የማትበገር፣ ጠንካራ፣ መሰረተ ጥሩ የተባለች ገጸ ባህሪ
ለወሲብ ግን ስትሸነፍ በአንድ አፍታ ክብረ ንጽህናዋን ስታጣ ያሳየናል ዘመን ድራማ።
.
ዘመንና አፈንጋጭ ወሲብ
.
የዘመን ድራማ የወሲብ ስካር ከዚህም ከፍ ይልና ሳዲዝም (sadism) ላይ ይወጣል፡፡ ሳዲዝም የወሲብ አይነት ሲሆን ከመደበኛው የወሲብ አይነት ወጣ ያለና በወሲብ አጋር ጋር ከሚደረግ ተላምዷዊ ተራክቦ ይልቅ በወሲብ አጋር በሚደርስ ስቃይና አካላዊ ጥቃት መርካት ነው፡፡ እንዲህ ያለባህሪ የተጠናወተው ሰው አፋጣኝ ህክምና ካላገኘ እስከ ነፍስ ማጥፋት የሚያደርስ ከባድ ማኅበራዊ ቀውስ የሚያስከትል የሥነ ልቦና ችግር ነው፡፡
.
ይህ በጥንቃቄ ሊያዝ የሚገባ ችግር በትውልዱ አእምሮ ውስጥ እንደ ጥሩ ነገር ለማስረጽ መሯሯጥ ዘመኖችን ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው፡፡ የዚህ ችግር ተጠቂ ዘመን ድራማ ላይ አዳነች የምትባል ገጸ ባህሪ ነው፡፡ አዳነች (ሃና ዮሐንስ) በተለያዩ የአእምሮ ቀውስ ውስጥ የምትገኝ ሲሆን አንዳንዴ ልጅቷ የሳይካትሪ ኮርስ መማሪያ መጻሕፍ ትመስለኛለች፡፡ ምክንያቱም አዳነች በናርሲስቲክ እንዲሁም ግራንዲየስ በተባለ የአእምሮ ቀውስ ውስጥም ያለች እንስት ነች፡፡
.
እንዲህ ያለ የአእምሮ መቃወስ ያለባቸው ሰዎች ከሚጠበቀውና ከሚታሰበው በላይ ክብርንና የበላይነት መፈለግ፣ ማንኛውም አይነት ኃይልን ለመቆጣጠር ምንም አይነት ዋጋ መክፈል፣ ክቡርና ክቡድ ሆኖ ለመታየት መጣር፣ በበነነ በተነነው እኔ እኔ እኔ ማለት፣ ሌሎችን በፍጹም ለመስማትና ለማዳመጥ አለመፈለግ፣ ይሉኝታ ቢስ፣ ጉረኛ፣ ራስ ወዳድ፣
በራስ መርካትና በውሸት በተገነባ ስብእና የእውነት እንደሆነ በማሰብ መኩራት…. ከብዙ በጥቂቱ ናቸው፡፡ የግራንዲስ ወይም የናርሲሲቲክ ወይም የሁለቱም ተጠቂ በብዛት በሀገራችን ቢታይም የሳዲዝሙ ግን የለም ባይባሉም ከባድ አይመስሉኝም፡፡
.
ቢሆንም ጉዳዩ በጥንቃቄ ሕክምናዊ ትኩረት እንጂ ድራማዊ ትኩረት ካገኘ ከመፍትሔው ይልቅ ያን ያህል እሳትና ውሃን በቅጡ በማይለዩ የአስራ ምናምን እድሜ ላይ ያሉ ወጣቶች ጉዳይና ተግባር የመሆን እደሉ ሰፊ ነው፡፡
.
እና ምን ይደረግ?
.
ይህን ሐሳብ ሳነሳ ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ሆኜ አይደለም፡፡ ተከታታይ ድራማ መጻፍና ማዘጋጀት በጣም አድካሚና ከባድ አቅምን እንደሚጠይቅ እኔም ጽፌ አይቼዋለሁ፡፡ ግን ከተሰራ አይቀር ለስፖንሰር ማጋበሻ ሳይሆን ለትውልዱ ጠብ የሚል ነገር መስራት ያስፈልጋል፡፡
.
አንዳንድ ጊዜ ደራሲው ያወቀውን ሁሉን መጻፍ አለበት ብዬ አላምንም፡፡ ሳዲዝም ስለታወቀ ስለ ሳዲዝም አይጻፍም፣ ሕገወጥ ነገር ስለተደረገ ሕገወጥ ነገር ሁሉ ለማሕበረሰቡ አይሰጥም፡፡ ሌላው ገጸባህሪን መለስ እያሉ ማየት ምን እንደሚመስሉ መገምገም ጥሩ ነው፡፡
.
በትክክል የምንጽፈው ድራማ ምን ይመስላል? ደራሲው የሚያስበው ድራማና ማሕበረሰቡ ድራማውን እንዴት እንዳየውና እንደተረዳው በተለያየ መንገድ ማረጋገጥ ግድ ነው፡፡
.
ድራማው ላይብዙ ሕገወጦች፣ የመረሩ ጨካኞች፣ የወሲብ ርሐብተኞች፣ እድሜ ያልገራቸው አዛውንቶች፣ ከባድ ምስጢረኞች እስከ ሰላሳኛው የድራመው ክፍል ታይተዋል፡፡ በተቃራኒው አፌን ሞልቼ ጀግና፣ ድንቅ፣ መቼም የማይረሳ ገጸህባሪ ጥራ ብባል ይከብደኛል። ከሴትም ከወንድ። ስለዚህ ስለ ሰይና ገጸባህርይ ቢታሰብበት? መቼም በአብዛኛው ጊዜ የእኛ ሞዴል የአሜሪካው ሆሊውድ ነው፡፡ አሜሪካውን ደግሞ እንኳን ያላቸውን ባህል፣ ታሪክ፣ እውቀትና እውነት አይደለም የሌላቸውን ታሪክና እውነታ፣ ምግባርና ባሕል ያላቸው
አስመስለው ይቀርጻሉ፡፡ ለምሳሌ አሜሪካውያን ያላሸነፉትን የቬትናምንና የሶማሌን ጦርነት ምድር ላይ ቢሸነፉም ሆሊውድ ላይ ግን የአሜሪካ የበላይነትና ልዕልና ነው የተጠበቀው፡፡ በሆሊውድ የአሜሪካውያንን ጀግንነት፣ ባህለ ብዙነትን፣ ለሰው አዛኝንና ሁሉን አዳኝነት ያሳዩናል፡፡


የኛዎቹ ፊልሞች ደግሞ ያሸነፍነው አድዋን በገዛ ድራማቻን በገዛ ቴሌቪዥናችን ሽንፈትን ያከናንቡናል፤ ጠብቀንና አክበረን ያቆየነውን ሥነምግባር በገዛ ፊልምና ድራማዎቻችን አፈር እናስበላዋለን፡፡ የሁለት ሺህ አመት የክርስትና ታሪክ ያለን እኛ፤ ከሳውዲ ቀድመን እስልምናን በክብር የተቀበልን እኛ ሃይማኖት የለሽ ሆነን በገዛ ቴሌቪዥናችን ትናንት እንደተፈጠረ ሕዝብ ታሪክ እንደ አዲስ ሲጻፍ ማየት ያመናል፡፡
Pages: 1